አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ህገወጡ ህወሓት በስልጣን ዘመኑ ለትግራይ ህዝብ ችግር ፈቺ ሳይሆን ቸግር ፈጣሪ እና አዋላጅ ነው አሉ የአዲግራት ከተማ ነዋሪዎች፡፡
በክልሉ አሁን የሰፈነውን ሰላም አስመልክቶ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ ያደረጉ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉት ፥ ከሶስት ሳምንት በፊት የትግራይ ወጣቶች ከቤታቸው ወጥተው አስፋልት ለመርገጥ 50 ሺህ ብር ይዘው መውጣት ነበረባቸው ፤ያንን ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ አካላቸው ጎድሎ በአካላቸው እንዲከፍሉ ይደረግ ነበር ነው ያሉት፡፡
ነዋሪዎቹ አክለውም ህገወጥ ቡድኑ ለ30 ዓመታት በስልጣን ላይ ሲቆይ የትግራይን ችግር ከመፍታት ይልቅ ችግር መፍጠር ላይ ሲሳራ ነበር ብለዋል፡፡
ህገወጡ ህዋሓት ባህሪው ሽፍታነት ነው፣ በትግራይ ህዝብ ላይ ቁማር መጫወት እንጂ ታግሎ ያመጣለት አንዳች ነገር የለም ያሉት ነዋሪዎቹ ህዝቡም ጦርነትን መቃወሙንና በየጊዜው ልጆቹን መሰዋዕት ማድረግ ሰልችቶታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በየጊዜው ጦርነት እያወጀ ወጣቶችን ለሞት፣ የትግራይ እናቶች ለሀዘን እና ለቅሶ እየዳረገ መሆኑንና ለህዝቡ የልማት ሥራ አለመስራቱን እንዲሁም በክልሉ ምንም አይነት የስራ እድል እንዳይኖር ማድረጉን አስረድተዋል።
የመንግስትን ሆደ ሰፊነት ንቆ ጦርነትን ለ 4ኛ ጊዜ ያካሄደው ቡድኑ የራሱን የፖለቲካ ርዕዮተ አለም ለማስቀጠል እንጂ ለትግራይ ህዝብ አስቦ እንዳልነበረም አብራርተዋል።
ጥቅሙ እና ስልጣኑ የተነካበት ሲመስለው ወጣቱን በግዳጅ ጭምር ለጦርነት እንደሚያዘምት የሚገልጹት ነዋሪዎቹ በሰላም ጊዜ ግን ህዝቡን አያስታውስም ነው ያሉት ፡፡
የክልሉ ህዝብ አሁን የሚሻው ሰላም እና መረጋጋት ነው ያሉት ነዋሪዎቹ፣ ወጣቱ መስራት፣ መማር እና መለወጥ እንደሚፈልግ ተናግረዋል።በመሆኑም አሁን የተገኘውን ሰላም ለማስቀጠል ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል፡፡
በእመቤት ሲሳይ