የሀገር ውስጥ ዜና

የትግራይ ህዝብ የለውጥ ፍላጎት ከፍተኛ ነው – ረዳኤ ኃለፎም

By betelhem girma

October 22, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ህዝብ የለውጥ ፍላጎት ከፍተኛ ነው አሉ የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የፖለቲካ ጉዳዮችና የህዝብ አደረጃት ዋና አስፈጻሚ  ረዳኤ ኃለፎም፡፡

 

ዋና አስፈጻሚው እንዳሉት የትግራይ ህዝብ ላለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት የተለያዩ ነፃነቶቹን ተነፍጎ ቆይቷል፡፡

 

ህዝቡ የእኔ በሚላቸው ሰዎች ተጫቁኖ መቆየቱን የጠቆሙት ዋና አስፈፃሚው፣ የሀሳብ ልዩነት እንደነውር ተቆጥሮ ህዝቡን በድንክ አስተሳሰብና አደረጃጀት ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርስበት የነበረው አካል ከጫንቃው ላይ ተላቆለታል ብለዋል፡፡

 

ባለአደራ አስተዳደሩም አስቸኳይ ለሆኑጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት መሠረታዊና የመንግሥት አገልግሎቶችን መልሶ ለማስጀመር እንዲሁም የህዝቡን ፍላጎት ለማሟላት በተጀመረው ፍጥነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 

ከነዋሪዎች ጋር በተደረጉ ውይይቶችና በተለያዩ አካባቢዎች በተደረጉ ጉብኝቶች የህዝቡ ተስፋና ወደ ሥራ የመመለስ ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 

ህዝቡ  ከነበረበት አስከፊ ጭቆና በመላቀቁ እና እየተፈጠረ ባለው ምቹ ሁኔታ ለክልሉ ልማትና ሰላም ግንባታ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አስገንዝበዋል፡፡

 

በግጭትና የተለያዩ ችግሮች ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮችን ከፌደራል መንግስት ጋር በትብብር በመፍታት ህዝቡ ወደ ልማት እንዲገባና አስፈላጊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ በየእለቱ እየተሰራ መሆኑን ረዳኤ ኃለፎም አስታውቀዋል፡፡

 

በቤተልሔም ግርማ