የሀገር ውስጥ ዜና

ሕገ ወጡ ህወሓት የትግራይ ሕዝብ ሀሳቡን በነጻነት እንዳይገልጽ አድርጎት ቆይቷል – አቶ ረዳኢ ኃለፎም

By Mikias Ayele

October 23, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕገወጡ ህወሓት የትግራይ ሕዝብ ሀሳቡን በነፃነት እንዳይገልጽ ሰርቷል አሉ የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የፖለቲካና ሕዝብ አደረጃጀት ዋና አስፈጻሚ ረዳኢ ኃለፎም።

አቶ ረዳኢ ኃለፎም ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ የባለአደራ አስተዳደሩ ከሕዝቡ ጋር በመወያየት ሐሳቦችንና አስተያየቶችን የመሰብሰብ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።

ባለአደራ አስተዳደሩ በትኩረት ከሚሰራባቸው ዋና ዋና አጀንዳዎች መካከል ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሕዝቡ ጥቅሙን ያስጠብቁልኛል ብሎ የሚያምንባቸውን መሪዎች በነፃነት መምረጥ እንዲችል ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባም ገልጸዋል።

በምርጫ ሂደት የሕዝቡን ነፃነት የሚገድቡ ተግባራትን ለመከላከል እንደሚሰራ ጠቁመው፤ ሕዝባዊ ጥቅም ከግልና ከቡድን ጥቅም በላይ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የመንግሥት አገልግሎቶችን ማስጀመርና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸው፤ ቀደም ሲል የተፈጸሙ ወንጀሎች በሕጋዊ ሂደትና አሠራር መጠናቀቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ከማይመለከታቸው አጀንዳዎች ርቀው ወደ ሕዝባቸው እንዲመለሱም ጥሪ አቅርበዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ሆን ተብሎም ሆነ ባለማወቅ የሚፈጸሙ የስም ማጥፋት ተግባራት መቆም እንዳለባቸው አሳስበው፤ ሠራዊቱ የትግራይ ሕዝብ ጠባቂ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።

ለትግራይ የሚጠቅም ሐሳብ ያለው ማንኛውም ወገን አስተያየቱን በነፃነት የሚያቀርብበት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርም እንደሚሠራ ገልጸዋል።

በግዛቸው ግርማዬ