አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ለ20 ዓመታት በመጓተቱ ሕዝብን ያስመረረውና በተደጋጋሚ ያልተጨበጠ የልማት ተስፋ ሲያስሰንቅ የዘለቀው የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት ዛሬ የምሥራች ይዞ መጥቷል።
በግንባታው መጓተት የተነሳ ቅሬታ ሲያሰሙ የነበሩ የጎንደርና አካባቢው ነዋሪዎች ዛሬ የዓመታት ጥበቃቸው ፍሬ ያፈራ መሆኑን የሚያበስር ዜና ሰምተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የተደረገው የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት ለአካባቢው ሕዝብ የልማት ጉዞ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።
የመገጭ ግድብ ታሪክ ግን የዛሬ ምርቃት ደስታ ብቻ አይደለም። ከጀርባው ለዓመታት የተራዘመ ጥበቃ፣ የተስፋ መቁረጥ፣ የሕዝብ ቅሬታና የመንግሥት አፈጻጸምን የሚያጠይቁ ድምፆች አሉ።
የመጠጥ ውሃ እጥረት፣ የመስኖ አቅም ውስንነትና በዝናብ ላይ ብቻ ተመርኩዞ የሚካሄድ ግብርና የአካባቢው ሕዝብ የሚጋፈጣቸው ተግዳሮቶች ነበሩ። በዚህ ሁኔታ የግድቡ ግንባታ ወሬ ደብዛው መጥፋትና መጓተት ማለት የግንባታ ጊዜ መራዘም ብቻ ሳይሆን፤ የሕዝብ የልማት ጥቅም መዘግየትም ነበር።
በግንባታው ሂደት የታዩት የቴክኒክ ችግሮች፣ የአዋጭነት ጥናት ውስንነቶችና የመሬት መንሸራተት ያሉ ተግዳሮቶች ሥራውን አጓተውታል የሚሉ ምክንያቶች ሲቀርቡ ዓመታትን አስቆጥረው ነበር። እውነተኛው ምክንያት ከህዝቡ የተሠወረ ሆኖ ለድፍን አስራ ስምንት ዓመታት ዘልቋል።
በግንቦት 2024 የፌዴራል አመራሮች ፕሮጀክቱን ገምግመው ሥራውን ለማፋጠን ቆርጠው ከተነሱ በኋላ የተቋራጭ ለውጥ፣ የቴክኒክ ችግሮች ግምገማና የተጠናከረ ክትትል ተደርጓል።
በነሐሴ 2026 የግንባታው ሂደት 94 በመቶ መድረሱ በፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተዘግቦ ነበር። ዛሬ ደግሞ የምርቃቱና የአገልግሎት መጀመሩ ዜና የዚህን ረጅም ጉዞ አዲስ የመጨረሻ ምዕራፍ እንደከፈተ ያመለክታል።
የግድቡ እውነተኛ ድል ግን በምርቃቱ መድረክ ላይ በሚታዩ ሥነ-ሥርዓቶች ብቻ አይለካም፤ በሕዝቡ ዕለታዊ ሕይወት ላይ በሚያመጣው ለውጥ ነው።
ፕሮጀክቱ ወደ 17 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬትን በመስኖ ለማልማት እንደሚያስችል መገለጹ፣ ለአካባቢው ግብርና ትልቅ ዕድል እንደሚከፍት ያመለክታል።
ገበሬው በዝናብ ላይ ያለውን ጥገኝነት እንዲቀንስ፣ በዓመት የሚያገኘውን የምርት መጠን እንዲያሳድግ፣ ገቢውን እንዲያሻሽልና የአካባቢው ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ ዕድል ይፈጥራል።
በዋናነት በውሃ ጥም ስትሰቃይ ለኖረችው ለጎንደር ከተማ እንዲሁም በአካባቢዋ ላሉ ከተሞች የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የሚኖረው አስተዋጽኦም ተጨማሪ ተስፋ ነው።
ዛሬ በጎንደርና አካባቢው የሚሰማው ደስታ የአንድ ግድብ መመረቅ ደስታ ብቻ አይደለም፤ የተራዘመ ጥበቃ ፍሬ ማፍራት፣ የተቋረጠ ተስፋ እንደገና መታደስና የልማት በር መከፈት የሚያስገኘው ስሜት ነው።
ይሁንና የዛሬው ደስታ የትናንቱን ቅሬታ እንዲያስረሳ ሳይሆን ከእሱ ትምህርት በመውሰድ የወደፊት ፕሮጀክቶች በጥናት፣ በብቃት፣ በጊዜና በተጠያቂነት እንዲፈጸሙ ማስቻል አለበት።
የመገጭ ግድብ ዛሬ ተመርቋል፤ የልማቱ ፈተና ግን አሁን ይጀምራል። ውሃው ወደ እርሻዎች ሲደርስ ምርት ሲጨምር፣ የገበሬው ገቢ ሲያድግና የከተማው ነዋሪ የውሃ እጥረት ሲቃለል ነው የዛሬው ምርቃት ሙሉ ትርጉሙን የሚያገኘው።
ለጎንደር ሕዝብ የሚያስፈልገው የግድቡን ምርቃት ማየት ብቻ ሳይሆን፤ የግድቡን ፍሬ በዕለት ተዕለት ሕይወቱ መቋደስ ነው። ያኔ የመገጭ ግድብ ከተራዘመ ፕሮጀክት ታሪክ ተሻግሮ የተስፋ፣ የምርታማነትና የዘላቂ ልማት ምልክት ይሆናል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በቶማስ ከበደ