የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የኃይል፣ የሰላም እና የጋራ ዕድገት ዋስትና ናት – አቶ ጌታቸው ረዳ

By Mikias Ayele

October 23, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የኃይል አቅርቦት፣ የሰላም እና የጋራ ዕድገት ዋስትና ናት አሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ።

12ኛው የጣና ፎረም በውቢቷ ባሕር ዳር በጣና ሐይቅ ዳርቻ “በአፍሪካ የሰላም መንገዶች፤ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦፖለቲካ ለውጥ” በሚል መሪ ሐሳብ ይካሄዳል።

በዛሬው ዕለትም በቀይ ባሕርና ምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ደኅንነት ዙሪያ በምሥራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኞች የጣና ልዩ መልዕክተኞች ጉባኤ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ አቶ ጌታቸው ረዳ እንዳሉት÷ በኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች የሚገኘው ለውጥ ለቀጣናው ሀገራት በፖለቲካና ጸጥታ ጉዳዮች ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል።

ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገች ያለች የ130 ሚሊዮን ዜጎች ሀገር መሆኗን በመጥቀስ፣ ዕድገቷ በቀጣናው ሀገራት ዘንድ በበጎ ጎኑ መታየት እንዳለበት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የቀጣናው የኃይል አቅርቦት ማዕከል ብቻ ሳትሆን የአካባቢው የኢኮኖሚ፣ የጸጥታ እና ደኅንነት ዋስትና መሆኗንም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በድንበር አካባቢ ለሰላምና ደኅንነት የምታደርገውን ጥረት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በውል ሊረዳው ይገባል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።