የሀገር ውስጥ ዜና

በድል የጸና፣ በቴክኖሎጂ የዘመነ ሠራዊት

By tigist gizachew

October 23, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድ ሀገር ሉዓላዊነትና የደህንነት ሁኔታ ከታሪካዊ ተሞክሮዎች፣ ከተቋማዊ አቅምና ከደህንነት ጋር ይያዛል።

ለ119 ዓመታት የኢትዮጵያ ዳር ድንበር በተጠንቀቅ ሲጠብቅ ለህዝቧ ደህንነት ሲዋደቅ ሉዓላዊነቷን ሲያስከብር የኖረው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በጀግኖች ደም እና አጥንት የጸና ታላቅ ተቋም ነው።

ውትድርና ለሀገር ሉዓላዊነትና ለህዝብ ክብር ህይወትን አሳልፎ ለመስጠት ቃል የሚገባበት የተከበረ ሙያ እንደመሆኑ የጀግናው የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት መገለጫ ከራሱ በላይ ለህዝብ ደህንነት መቆሙ ነው።

ሠራዊቱ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ የረጅም ጊዜ ልምድ ያካበተ ተቋም ሲሆን፣ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የሕዝብን ደህንነት መጠበቅ ተልዕኮ አለው።

በወታደራዊ ጥበቡና ብቃቱ ሠራዊቱ በተሰማራበት ግንባር ሁሉ በአይበገሬነቱ እና በድል አድራጊነቱ ተመስክሮለታል፡፡

ከሰላም ማስከበር ተልዕኮ ስኬት አልፎ በኮሪያ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ ወታደሮች ያደረጉት ተሳትፎ ሠራዊቱ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ካስመዘገባቸው ወታደራዊ ጀብዱዎች መካከል ይጠቀሳል።

የሠራዊቱ በተለያዩ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የመሳተፍ  ተሞክሮዎች የወታደራዊ ሥልጠና፣ የተቋማዊ ቅንጅትና የዓለም አቀፍ ትብብር አስፈላጊነትን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡

ታሪክን በደምና በአጥንት ከመጻፍ አልፎ፣ የነገዋን የበለፀገች ኢትዮጵያ በእውቀትና በቴክኖሎጂ ምሰሶ ላይ የሚያቆም ግዙፍ ኃይል በመሆን የሀገር ጋሻ ሆኖ ቀጥሏል።

ታሪክን መስራት ብቻ ሳይሆን ከዘመኑ ጋር አብሮ መዘመንን ሀብት ያደረገው የመከላከያ ሰራዊቱ ዘመኑን የዋጀና በቴክኖሎጂ የዘመነ አስተማማኝ ኃይል ሆኖ ተገንብቷል፡፡

ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሥራዎች ሠራዊቱ በሥልጠና፣ በአደረጃጀት እና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ተጨባጭ ለውጦችን አስመዝግቧል።

የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ቴክኖሎጂ፣ ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓቶች እንዲሁም የዲጂታል ግንኙነት ሥርዓቶች የተቋሙ መገለጫ ሆነዋል። በዚህም የሰለጠነ የሰው ሀብትን ከዘመን አመጣሽ መሳሪያዎች ጋር አቀናጅቶ በመስራት ወታደራዊ ሳይንሱን አዘምኗል።

ከምርምር ተቋማት ጋር በመቀናጀት፣ ጥልቀት ያለው የዓላማ ውህደት እና ከፍተኛ የስትራቴጂካዊ ምልከታ አቅም ያለው ተማሪና አዳጊ ተቋም መገንባት ተችሏል።

ሀገሪቱ በወደፊቱ ዓለም አቀፍ ውድድር ራሷን ለማዘጋጀት የምትወስዳቸው ታላላቅ ርምጃዎች ይህንን ተቋም ይበልጥ የሚያጠናክሩ ናቸው።

በምህረት ደምሴ