የሀገር ውስጥ ዜና

ዘመናዊ የደኅንነት አቅምና ጠንካራ ተቋማት የዘላቂ ሰላም መሠረት

By tigist gizachew

October 24, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድ ሀገር ዘላቂ የልማትና የብልፅግና ጉዞ የሚመሰረተው ባለፈ ታሪኳ እና በታደለችው የተፈጥሮ ሀብት ብቻ ሳይሆን ሰላምን ማስፈን የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የዜጎችን መብትና ደኅንነት ማስጠበቅ የሚችሉ ጠንካራና ተጠያቂ ተቋማትን በመገንባትም ጭምር ነው።

ለዚህም ኢትዮጵያ የምትመኘውን የልማት፣ የሰላምና የብልፅግና ግብ ለማሳካት የፀጥታና የፍትሕ ተቋማትን የማጠናከር ሥራ ወሳኝ በመሆኑ በከፍተኛ ትኩረት እየሰራችበት ትገኛለች።

ይህ ትኩረት ዜጎች በደህንነት የሚኖሩበት፣ በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች በነፃነት የሚሳተፉበትና መብታቸው የሚከበርበት ሁኔታ መፍጠርንም ይጨምራል።

ይህንን ለማረጋገጥ የመከላከያ ሠራዊት፣ የፖሊስ፣ የመረጃና ደኅንነት ተቋማት፣ የፍትሕ አካላትና የሰላም ግንባታ ተቋማት በሕግ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት፣ በገለልተኝነትና በሙያዊ ሥነ-ምግባር መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

የእነዚህ ተቋማት ሪፎርም የሰው ኃይልን በማሠልጠን፣ የአመራር ብቃትን በማሳደግ፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀምና በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ አሰጣጥን በማጠናከር የተቋማትን የሥራ ውጤታማነት ለማሻሻል ያለመ ነው።

የተቋማት ጥንካሬ የሚለካውም በመዋቅርና በሀብት ብዛት ብቻ ሳይሆን በሚያስገኙት ተጨባጭ ውጤትና በሕዝብ እምነት ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ሉዓላዊነትና የድንበር ደኅንነት የመጠበቅ ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነት ያለው ብሔራዊ ተቋም እንደመሆኑ ሠራዊቱ ያለውን ታሪካዊ ሀላፊነት በማስቀጠል የዘመኑን የደኅንነት ፈተናዎች መመከት እንዲችል በሙያዊ ሥልጠና፣ በቴክኖሎጂ፣ በምርምርና በሎጂስቲክስ ዝግጁነት በሚገባ ተጠናክሯል፡፡

የድሮን ቴክኖሎጂን፣ የዲጂታል መረጃ ሥርዓቶችንና የምርምር አቅምን ማሳደግ በዘመናዊ የደኅንነት ዘርፍ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።

በተጨማሪም የሀገር ውስጥ የቴክኖሎጂ ምርትና የሙያተኞች ልማት በውጭ ቴክኖሎጂ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስና የሀገርን የፈጠራ አቅም ለማሳደግ ዕድል ይፈጥራል።

በሀገር ውስጥ የድሮን ቴክኖሎጂን ለማሳደግ የተወሰዱ ርምጃዎችን ጨምሮ ተቋሙን የወቅቱን የመከላከል ስልት የተላበሰ ብቁ እና ዝግጁ ለማድረግ የተደረጉ ጥረቶች በምርምር፣ በምህንድስና፣ በሙያተኛ ልማትና በኢንዱስትሪ ግንባታ ላይ ቴክኖሎጂን ከመጠቀም ወደ መፍጠርና ማምረት የሚደረገውን ሽግግር በእጅጉ የሚያግዙ ናቸው።

የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት የሚኖራቸው የረጅም ጊዜ ስኬት እንዲሁም በቴክኖሎጂና በሥልጠና መብቃት በተለዋዋጩ ዓለም የሀገርን ሉዓላዊነት አስከብሮ ለተተኪ ትውልድ ለማስረከብ ሕግን እና የዜጎችን መብት ለማስከበር ተጠያቂነትን በማረጋገጥና የሕዝብ እምነትን ለማግኘት የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው።

የመከላከያ ሠራዊት፣ የፖሊስ፣ የመረጃና ደኅንነት ተቋማት፣ የፍትሕ አካላትና የሰላም ግንባታ ተቋማት በተቀናጀ መንገድ መሥራታቸው ለሀገር ዘላቂ ልማት እና መረጋጋት ወሳኝ ነው።

በሀገር መከላከያ ሰራዊት የተደረገው ሪፎርም ውጤትም በተግባራዊ ብቃት፣ በተቋማዊ ቅንጅት እና በቴክኖሎጂ ፈጠራ በመገለጥ ላይ ይገኛል።

ከጠንካራ ተቋማት፣ ከዘላቂ ሰላም፣ ከሕግ የበላይነትና ከዜጎች እምነት ጋር የተያያዘው የኢትዮጵያ የልማትና የብልፅግና ርዕይ ተቋማት በዕውቀት፣ በሙያዊ ሥነ-ምግባርና በተጠያቂነት ሲመሩ፣ የሀገርን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ ባሻገር የልማት ሂደቱን የሚያግዝ የተረጋጋ ምህዳር ለመፍጠር ያላቸው ሚና ይጎለብታል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በምሕረት ደምሴ