አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ክንድ ከዓድዋ እስከ ዛሬዋ ዘመናዊት ኢትዮጵያ ድረስ የሀገራችንን ሉዓላዊነት እና ነፃነት አስከብሮ ያስቀጠለ፤ ለጠላቶች መቅሰፍት፣ ለሕዝቡ ደግሞ ጽኑ መከታ የሆነ ታላቅ የጀግንነት መገለጫ ነው።
የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሠ በአንድ ወቅት ስለ ኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንዲህ ብለው ነበር÷ ‘እኛ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የቁርጥ ቀን ልጆች እያለን ኢትዮጵያን መበተን አይቻልም፤ አይታሠብምም’ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ድንበር የማይገድበው የሰላምና የልማት ኃይል የሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሀገርን በሉዓላዊነት፣ በሰላም እና በድኅንነት ለመጠበቅ የታሪክ ምትክ የሌለው ሚና የሚያበረክት ብርቱ ተቋም ነው።
ለጠላት መቅሰፍት የሆነው የኢትዮጵያ ሠራዊት ክንድ ጥንካሬ በቃላት ድርደራ ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን፤ በታሪክ ምዕራፎች ውስጥ ጠላቶቹ ላይ ባስመዘገባቸው የውጊያ ውሎዎች ያስመሰከረው እውነት ነው።
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት መሠረት የሆነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጀግኖች አባቶቹ ያወረሱትን አኩሪ የጀግንነት ገድል፤ ዛሬ ዘመኑ በደረሰበት ወታደራዊ የጦር ሳይንስ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እና በዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ቅንጅት የሀገሩን ከፍታ እያስቀጠለ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ በታሪኳ አያሌ ፈተናዎችን አልፋ፤ በነጻነቷ እና በሉዓላዊነቷ ኩሩ ሆና ለመቆሟ ዋናው መሠረትም የሠራዊቱ የማይናወጥ ክንድ እና መሥዋዕትነት ነው፡፡ ይህ ሠራዊት የትናንት ታሪካችን ኩራት፣ የዛሬ ሰላማችን እና የነገ ተስፋችን መሠረት ሆኖ ይቀጥላል፡፡
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በትዕግስት ግዛቸው