የሀገር ውስጥ ዜና

በመደመር መንግሥት ለከተሞች ልማት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው – አፈ ጉባኤ አህመድ ሽዴ

By sosina alemayehu

October 25, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በመደመር መንግሥት ለከተሞች ልማት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው አሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አህመድ ሽዴ፡፡

የቀጨኔ–አምባሳደር–ጊዮን-ኢሬቻ–ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ልማት በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡

አፈ ጉባዔ አህመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የወንዝ ዳርቻ ልማቱ አካበቢውን ምቹ እና አረንጓዴ አድርጎ በማድረግ የስራ አድል ፈጥሯል፡፡

በወንዝ ዳርቻው የተሰራው የመሰረተ ልማት በከፍተኛ ጥራት መሰራቱን ጠቅሰው፤ የእግረኛ እና የተሸከርሪ መንገዶቹ በከፍተኛ ጥራት መሰራታቸውን አመልክተዋል፡፡

በአጠቃላይ የተሰራው የመሰረተ ልማት ከፍተኛ ጥራት ያለው ነው ያሉት አፈ ጉባዔ አህመድ ሽዴ የወንዝ ዳርቻው ልማት አካባቢውን ወደ ተሟላ የልማት አቅም መቀየሩን ገልጸዋል፡፡

የተሰራው ስራ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በከፍተኛ ደረጃ ያሳደገ መሆኑን አንስተው፤ ምቹ የኑሮ ሁኔታ በመፍጠር ከፍተኛ የስራ ዕድል ማምጣቱን አስረድተዋል፡፡

ወንዞቻችን ሲለሙ ወደ ድርጁ የልማት አቅም ተቀይረው ለህብረተሰቡ ከፍተኛ አገልግሎት እንደሚሰጡ የታየበት ነው ብለዋል፡፡

የመንግሥት፣ የህዝብና የግሉ ዘርፍ ትብብር የታየበት ስራ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

የወንዝ ዳርቻ ልማቱ የከተማዋን ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ የገለጠ መሆኑን ጠቁመው፤ በመደመር መንግሥት ባለፉት ዓመታት ለከተሞች ልማት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡