አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ህዝብ በህገ ወጡ ህወሓት የጦርነት አዙሪት የነበረውን ሁሉ አጥቷል አሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ።
119ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን “የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬው ዕለት እየተከበረ ነው።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ህገ ወጡ ህወሓት አራት እንቅፋት የመታው ፍጡር ነው ብለዋል።
ቡድኑ በዘመቻ ህግ ማስከበር፣ በዘመቻ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት፣ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትን በወለደው ዘመቻ በሁሉም ተመትቶ ለአራተኛ ጊዜ ወደ ቆቦ፣ ሰቆጣ፣ ላሊበላ፣ ተኩለሽ እና አካባቢው መጥቶ ተመትቷል ብለዋል። አሁን ወደ ባልደረባው ሻዕቢያ የሄደው ህገ ወጡ ህወሓት አምስተኛ እድል እንዲኖረው አናደርገውም ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ የትግራይ እናቶች፣ ወጣቶች፣ ሽማግሌዎች፣ በህገ ወጡ ህወሓት የጦርነት አዙሪት የነበራቸውን ሁሉ አጥተዋል ሲሉ ገልጸዋል።
ልጆቻቸውን በጉልበት እየተነጠቁ ወደ ጦርነት በመማገድ ትውልድ እንዲያጡ እና በሀዘን እንዲጎሳቆሉ በማድረግ የትውልድ ቅብብሎሽ ተዛብቷል ነው ያሉት።
ህዝቡ የነበረውን ጥሪት አጥቶ እርዳታ ጠባቂ መደረጉን ጠቅሰው፤ አሁን ህዝቡን ከህገ ወጡ ህወሓት የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ህገ ወጡ ህወሓት ‘በሁለት ሳምንት ኢትዮጵያን እቀብራለሁ ብሎ ተነስቶ’ ሁለት ሳምንት ሳይሞላው ላይመለስ መቀበሩን ገልጸዋል።
ትግራይ ክልል አዳዲስ ሀሳቦች፣ አዳዲስ አመራሮች፣ ሰላም እና ልማት እንደሚፈልግም አብራርተዋል። #ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በእመቤት ሲሳይ