አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17 ፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ጥቅምት 18 እና 19፣ 2019 በሞስኮ የሚካሄደው 3ኛው የሩሲያ – አፍሪካ ጉባኤ በሩሲያ እና በአፍሪካ አህጉር መካከል ያለውን የጂኦፖለቲካዊ ና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ኩነት ነው።
በፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሰብሳቢነት በሚከናወነው በዚህ መድረክ ላይ ከ54 የአፍሪካ ሀገራት መካከል 48ቱ ይሳተፋሉ፤ ይህም የጉባኤውን ክብደት የሚያሳይ ነው።
በጉባኤው የሁለትዮሽ ውይይቶች እና ጠቅላላ ጉባኤዎች የሚካሄዱበት ሲሆን፣ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የሩሲያ–አፍሪካ የኢኮኖሚ እና ሰብዓዊ ፎረም ይካሄዳል።
ይህ አህጉራዊ መድረክ በተለይ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል እና የብሪክስ አባል ለሆነችው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ትርጉም አለው። የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ አህጉሪቱ በዓለም አቀፍ መድረኮች፣ በተለይም በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ተገቢውን ውክልና እንድታገኝ ከሩሲያ ጋር በትብብር እየሰራች ትገኛለች። ከዘመነ ዓድዋ ጀምሮ የጸናው ታሪካዊ ወዳጅነት በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ በሚያስችል የወታደራዊና ቴክኖሎጂ ትብብርም የበለጠ እየተጠናከረ መጥቷል።
ከወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ባሻገር ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር በግብርናው ዘርፍ የማዳበሪያ አቅርቦትን ለማሳደግ፣ በዲጂታል መሠረተ ልማት ግንባታ እና የኒውክሌር ኃይልን ለሰላማዊ አገልግሎት ለማዋል የሚያስችሉ በርካታ የትብብር ስምምነቶችን ተግበራዊ እያደረገች ትገኛለች። በአጠቃላይ የሞስኮው ጉባዔ ኢትዮጵያ በዓለም የኃይል አሰላለፍ ውስጥ አህጉራዊ መሪነቷን የምታረጋግጥበትና ብሔራዊ ጥቅሟን የምታስከብርበት ወሳኝ መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃል።
የሩሲያ–አፍሪካ ጉባኤ በሩሲያ እና በአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት መካከል ያለውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የደህንነት እና የሰብዓዊ ትብብር ለማስፋፋት የሚካሄድ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ መድረክ ነው።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ በሶስና አለማየሁ