አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር መከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያን ከውጭ ጠላቶች እየተከላከለ እና የውስጥ አፍራሽ ኃይሎችን እየመከተ ሀገር እንድትጸና አድርጓል አሉ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው።
በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
በሰልፉ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር አንድነትንና ሉዓላዊነትን ለማጽናት እያደረገ ያለውን ተጋድሎ የሚደግፍ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዚህም በማይነጥፈው የመከላከያ ሠራዊታችን የጀግንነት ተጋድሎ የሀገራችን ክብር ከፍ እናደርጋለን፤ የኢትዮጵያ ጠላቶችን እየደመሰስን ሰንደቅ ዓላማችን ከፍ እናደርጋለን፤ መከላከያ ሠራዊታችን፣ የፌዴራል እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች ለከፈሉት ዋጋ ክብር እንሰጣለን የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል።
በተጨማሪም መንግሥት ለሰላም መስፈን የሚወስዳቸውን እርምጃወች እንደግፋለን፤ የሀገራችን አንድነት በፀረ ሰላም ኃይሎች ሴራ አይደናቀፍም፤ ሀገርን ለማፅናትና ለማበልፀግ ከመንግሥት ጎን እንሰለፋለን፤ መከላከያ ሠራዊታችን የኅብረ ብሔራዊነታችን ማሳያ አርማችን ነው ሲሉ ለሀገር ሰላም እና ለመከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የሀገር ምልክት ለሆነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፋችንን ስንገልጽ ዳግም በሰንደቅ ዓላማችን ፊት ቃል እየገባን፣ የሠራዊቱን የምንጊዜም ጀግንነት እያረጋገጥን ነው ብለዋል።
ሠራዊቱ ኢትዮጵያን ከውጭ ጠላቶች እየተከላከለ፤ የውስጥ አፍራሽ ኃይሎችንም እየመከተ ሀገር እንድትጸና እያደረገ ዘልቋል ሲሉ ገልጸዋል።
ባዳዎች እና ባንዳዎች ሀገር ለማፍረስ እያደረጉት ያለውን ተልዕኮ በመመከት ሀገር የማጽናት ተልዕኮውን በጀግንነት መወጣቱን አንስተዋል።