የሀገር ውስጥ ዜና

ለሀገርና ለሉዓላዊነት ዘብ የሕዝብ ደጀንነት

By sosina alemayehu

October 27, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር መከላከያ ሠራዊት በተፈተነባቸው ሜዳዎች ሁሉ በጽናት አልፎ ድልን የተቀዳጀ ሀገርን ለሁለንተናዊ ከፍታ የሚያበቃ የድል ሠራዊት ነው። ይህ ሠራዊት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በጽናት ለመጠበቅ፣ ዘላቂ ሰላምና ጸጥታን ለማስፈን እንዲሁም የህዝቡን ሁለንተናዊ ደህንነት ለማረጋገጥ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት የሚያስችለውን ቁመና ገንብቷል።

ሠራዊቱ ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትን ለመፈታተን የሞከሩ የውስጥ ባንዳዎችን እና የውጭ ጠላቶችን አምክኗል።

ሠራዊቱ በጉዞው ሁሉ ህዝባዊነቱን እያረጋገጠ የመጣ ሲሆን፤ ህዝቡም የሠራዊቱ ደጀን መሆኑን በተለያየ መንገድ ይገልጻል።

ባለፉት ቀናት በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የታየው ህዝባዊ ሰልፍም የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጠንካራ የህዝብ ደጀን እንዳለው ያረጋገጠ ነው።

ዛሬ በባህርዳር ከተማ የተካሄደውን ሰልፍ ጨምሮ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ህዝብ አደባባይ በመውጣት ለዘላቂ ሰላም ያለውን ጽኑ ፍላጎት እና ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ጠንካራ ደጀን መሆኑን ያረጋገጠበትን መልዕክት አስተላልፏል።

በሰልፎቹ ላይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸው ሁሉም ወገን የጸና የሰላም ፍላጎት እንዳለውና የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ሌሎች የጸጥታ አካላት ለሰላም መስፈን ለሚያደርጉት ጥረት ያለውን  አጋርነት ያሳየ ነው።

‘የኢትዮጵያ ጠላቶችን እየደመሰስን ሰንደቅ ዓላማችን ከፍ እናደርጋለን፤ መከላከያ ሠራዊታችን፣ የፌዴራል እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች ለከፈሉት ዋጋ ክብር እንሰጣለን፤ መንግሥት ለሰላም መስፈን የሚወስዳቸውን እርምጃወች እንደግፋለን፤ የሀገራችን አንድነት በፀረ ሰላም ኃይሎች ሴራ አይደናቀፍም በማለት ህዝቡ መልዕክቱን አስተላልፏል።

በተጨማሪም ሀገርን ለማፅናትና ለማበልፀግ ከመንግሥት ጎን እንሰለፋለን፤ መከላከያ ሠራዊታችን የኅብረ ብሔራዊነታችን ማሳያ አርማችን ነው፤ በማይነጥፈው የመከላከያ ሠራዊታችን የጀግንነት ተጋድሎ የሀገራችን ክብር ከፍ እናደርጋለን፤ የሀገራችንን ሰላም ለማወክ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር የተሰለፉ ኃይሎችን በፅኑ እናወግዛለን በማለት አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡

ከግድቡ ወደ ወደቡ እንሸጋገራለን እና የባሕር በር ባለቤትነታችን በልጆቿ መሥዋዕትነት እውን ይሆናል በማለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እውን መሆን የድርሻቸውን ለመወጣት ያላቸውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።

በነቂስ በመውጣት በሰልፎቹ የተሳተፈው ሕዝብ ለሀገርና ለሠራዊቱ ያለው ደጀንነት ዛሬም በጽናት እንደሚቀጥል አሳይቷል።  ይህ ሕዝባዊ ወኔና እልህ፣ የውስጥና የውጭ ጠላቶች በሐሰተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሊያናውጡትና ሊከፋፍሉት ለሞከሩት አፍራሽ ባንዳዎች በአንድ ድምፅ የተሰጠ የማያወላውልና ቁርጠኝነት የተሞላበት የድል ምላሽ ነው።