የሀገር ውስጥ ዜና

የመከላከያ ሠራዊት አባላት በትግራይ ክልል የአርሶ አደሮችን የደረሰ ሰብል ሰበሰቡ

By sosina alemayehu

October 27, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመከላከያ ሠራዊት ምዕራብ ዕዝ አብዲሳ አጋ ክፍለ ጦር አባላት በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን አዴት ወረዳ ለሚገኙ አቅመ ደካማ አርሶ አደሮች የጤፍ ሰብል በመሰብሰብ ድጋፍ አድርገዋል።

የክፍለ ጦሩ አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ገዛኸኝ በቀለ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ፥ ሠራዊቱ የሕዝብ ልጅ በመሆኑ የሀገርን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባለፈ ከሕዝቡ ጋር ያለውን ትስስር በተግባር ማሳየት አለበት።

በዚህም መሠረት ሠራዊቱ በተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና የሚገኘውን ማኅበረሰብ ችግር በመጋራት የሕዝብ መከታነቱን በተግባር እያረጋገጠ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

የአባይ ሬጅመንት አዛዥ ሻምበል አማረ ሙሉነህ በበኩላቸው፣ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች በተለያዩ ምክንያቶች ሰብላቸውን በወቅቱ ለመሰብሰብ ሊቸገሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፣ ይህንን ችግር ለማቃለልና የተትረፈረፈው ምርት እንዳይባክን ርብርብ መደረጉን ገልጸዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸው አርሶ አደሮች ወይዘሮ ማሞ ገብረየሱስና አቶ ደሳለኝ ገረንቼል በበኩላቸው፣ በአካባቢያቸው የተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

አያይዘውም የደረሰውን የጤፍ ሰብል በወቅቱ ለመሰብሰብ ያገኙት የሠራዊቱ እገዛ ትልቅ እፎይታ እንደሰጣቸው በመናገር ላደረጉላቸው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን የመከላከያ ሠራዊት ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል።