የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያና ሩሲያ ትብብር ለአፍሪካ ሰላምና ልማት

By Melkam Fekadu

October 28, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መድረክ የምታሳየው አካሄድ እና ሚዛናዊነት ዛሬም ድረስ የቀጣናውን ሰላም አጽንቶ ለማቆየት ወሳኝ ምሰሶ ሆኖ ቀጥሏል።

ከዚህ አውድ አንጻር፣ ከሩሲያ ጋር ያላት ታሪካዊ እና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት በወታደራዊ፣ በቴክኖሎጂ እና በሰላም ማስከበር ዘርፎች እጅግ የጎላ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀጣና የዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆኗ ብቻ ሳይሆን፤ ከሩሲያ ጋር ያላት ግንኙነት ረጅም ዘመንን ያስቆጠረና የጸና ነው።

በዲፕሎማሲው መስክ ኢትዮጵያ ከሞስኮ ጋር ያላት ቀረቤታ በአህጉሪቱ ካሉ ሀገራት አንጻር ልዩ መልክ አለው።

ይህ ግንኙነት በመከባበር፣ በእኩልነት እና የጋራ ጥቅምን ባስጠበቀ መልኩ የተገነባ በመሆኑ፤ ለሁለቱም ሀገራት ወዳጅነት የጸና መሰረት ሆኗል።

ሞስኮ በአፍሪካ ቀጣና ደህንነት እና የፖለቲካ ትብብር ጉዳዮች ዙሪያ ስትመክር፣ ኢትዮጵያን እንደ ዋና እና አስተማማኝ አጋሯ ትመለከታለች። የሁለቱ ሀገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጋራ መግባባትን ያጠናከረና ለአፍሪካ ሰላም ቀጣይነት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው።

በዚህ ዘመን ቴክኖሎጂ እና ወታደራዊ አቅም የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የላቀ ድርሻ አላቸው።

ኢትዮጵያና ሩሲያ በወታደራዊና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላቸው ትብብር እያደገ መጥቷል። የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሽግግርን፣ የሠራዊት አቅም ግንባታ እና የባለሙያዎች ስልጠና ጨምሮ በበርካታ ዘርፎች የተደረጉ ስምምነቶች የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግረውታል።

ሁለቱ ሀገራት በዲፕሎማሲው፣ በወታደራዊ ቴክኖሎጂ እና በደህንነት ዘርፍ የገነቡት ጠንካራ ትስስር በቀጣናው ሁለንተናዊ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።

ይህ ትብብር ሀገሪቷ የውጭ ኃይሎችን ጥቃት ለመመከት ብቻ ሳይሆን፣ በምስራቅ አፍሪካ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ያላትን አቅም ከፍ የሚያደርግ ነው።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላም እንዲሰፍን ያደረገችው ተጋድሎ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተደበቀ አይደለም።

በሱማሊያ፣ በሱዳን እና በሌሎችም የአህጉሪቱ ሀገራት ሰላምን ለመመለስ የኢትዮጵያ ሠራዊት የከፈለው መስዋዕትነት፣ የሀገሪቷን ሰላም ወዳድነት በግልጽ ያሳያል።

በደህንነት ዙሪያ ሁለቱ ሀገራት ያላቸው አጋርነት ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትን፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን እና ህገ-ወጥ የሰዎች እና የመሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ ሚና አለው።

የሩሲያ መንግሥት ኢትዮጵያ የምታደርገውን የሰላም ጥረት እንደ አህጉራዊ መረጋጋት ዋስትና በመቁጠር በበጎ እይታ ሲደግፈው ቆይቷል።

የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ግንኙነት ጊዜውን የዋጀ፣ በወንድማማችነት መርህ በጋራ ልማት እና በአህጉራዊ የጸጥታ ማዕቀፍ የተሳሰረ ነው።

ሁለቱ ሀገራት ለረጅም ዘመናት በዲፕሎማሲው መስክ የፈጠሩትና ጠብቀው ያኖሩት ጠንካራ ትስስር በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ላይ ያላቸውን ጽኑ አቋም ያሳያል።

ይህ ታሪካዊ ወዳጅነት ወደፊትም የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች የጋራ ጥቅም የሚያረጋግጥና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ሚዛንን የሚያጠናክር ነው፡፡

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በመልካም ፈቃዱ