የሀገር ውስጥ ዜና

ታግዶ የቆየው የትግራይ ቴሌቪዥን በአዲስ ስያሜ ፍቃድ ተሰጠው

By sosina alemayehu

October 29, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ታግዶ የቆየውን የትግራይ ቴሌቪዥንን በአዲስ ስያሜ ፍቃድ መስጠቱን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቀደም ሲል ታግዶ የነበረውን “የትግራይ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ” የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ “የትግራይ ሚዲያ ኮርፖሬሽን” በሚል አዲስ ስያሜ በዛሬው ዕለት ማደሱን አስታውቋል።

ባለሥልጣኑ እንዳስታወቀው ፥ ከዚህ ቀደም የትግራይ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 የሚቃረኑ፣ ብሔራዊ ጥቅምን የሚጻረሩ፣ ጽንፈኝነትን የሚያበረታቱ እና የአገርንና የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ይዘቶችን ሲያሠራጭ በመገኘቱ ፈቃዱ ታግዶ መቆየቱ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር ቀደም ሲል ተቋሙ የጦርነትና የጥፋት ተልዕኮ ማስፈጸሚያ ሆኖ እንደነበር አምኖ፤ አሁን ላይ ክልሉን የሚመራው አስተዳደር የክልሉን ሰላምና መረጋጋት በማረጋገጥ የሕዝብ ድምፅ በመሆን አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት በማሰብ “የትግራይ ሚዲያ ኮርፖሬሽን” በሚል አዲስ ስያሜ ፈቃድ እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንም የቀረበውን ጥያቄ ከመገናኛ ብዙኃን አዋጅ አንፃር በመመርመር ተገቢነት ያለው መሆኑን በማመን ጥያቄውን መቀበሉን የባለስልጣኑ መረጃ ያመለክታል።

ባለሥልጣኑ ለተቋሙ አዲስ የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ የሰጠ መሆኑን እያሳወቀ፣ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ለሚዲያ ኮርፖሬሽኑ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።