አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ ወደፊት ወደ አፍሪካ አህጉር በሚመጣበት ጊዜ የአፍሪካ ሕብረት መዲና የሆነችው አዲስ አበባ መድረኩን ለማስተናገድ ዝግጁ ናት አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ3ኛው ሩሲያ – አፍሪካ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ፥ አዲሱ የሁለትዮሽና የአህጉራዊ ትብብር የድርጊት መርሃ-ግብር ግልጽ ተግባራትንና የተወሰኑ የጊዜ ሰሌዳዎችን አካቶ መውጣት አለበት ብለዋል።
በዚህም ጉባዔው ወደ አፍሪካ አህጉር በሚመጣበት ወቅት የአፍሪካ ሕብረት መዲና የሆነችው አዲስ አበባ መድረኩን ለማስተናገድ ታላቅ ክብር እንደሚሰማት እና ዝግጁ መሆኗን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በሀገራት መካከል ያሉ የክፍያ መንገዶች የንግድ እንቅስቃሴዎችን ቀላልና ርካሽ ማድረግ እንዳለባቸው ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ሩሲያ ለወዳጅነታቸው ለሚኖራት ቁርጠኝነት ከፍተኛ ቦታ እንደምትሰጥና በበኩሏ የሚጠበቅባትን ኃላፊነት እንደምትወጣ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ድርድርን የተከተሉ መፍትሄዎችን፣ አፍሪካ-መር ድርድሮችንና የተባበሩት መንግስታት ቻርተር ለእያንዳንዱ ሀገር በወጥነት ተግባራዊ መሆን አለበት የሚለውን መርህ የምትደግፍ መሆኑን አንስተዋል።
የመደመር ፍልስፍናችን እያንዳንዱ አጋር የሚሰጠው ነገር እንዳለው ያሳያል ብለው ከ130 ዓመታት በፊት የሩሲያ የሕክምና ዕውቀት ወደ አማርኛ ተተርጉሟል። ዘንድሮ ደግሞ ‘መደመር’ መጽሐፍ ወደ ሩስኪ ተተርጉሟል፤ ዕውቀት በሁለቱም አቅጣጫ እየተንቀሳቀሰ ነው ሲሉ አመልክተዋል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በሶስና አለማየሁ