አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የኢንተርፖል ግሎባል አካዳሚ ኔትወርክን መቀላቀል የሚችልበትን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል እና የኢንተርፖል ዋና ፀሐፊ ቫልደሲ ኡርኪዛ በጋራ ተፈራርመውታል፡፡
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በኢንተርፖል ግሎባል አካዳሚ ኔትወርክ ውስጥ በይፋ መቀላቀሉን ገልጸው፤ ስምምነቱ በሁለቱ ተቋማት ታሪክ ውስጥ አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚከፍት ነው ብለዋል፡፡
ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ፖሊስ ተቋማዊ ልማት ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ፣ የትምህርት ደረጃዎችን ከዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ጋር ለማጣጣም የሚያግዝ እና ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ሀብት ሆኖ እንደሚያገለግልም ጠቁመዋል።
ሀገራት ለብቻቸው ዓለም አቀፍ ወንጀልን መዋጋት እንደማይችሉ ጠቁመው፤ ስምምነቱ የፌደራል ፖሊስ የተሻለ የመረጃ ልውውጥ፣ ዘመናዊ የወንጀል ምርመራ ቴክኖሎጂዎችን እና የማስተባበር ርምጃዎችን እንዲጠቀም የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ኢንተርፖል ቀደም ሲል በቨርቹዋል አካዳሚው በኩል ለኢትዮጵያ የፖሊስ መኮንኖች ለሰጣቸው የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የሚፈጽሙ ወንጀለኞችን አድኖ በመያዝ ለፍርድ በማቅረብ ረገድ ላበረከተው የጎላ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢንተርፖል ዋና ፀሐፊ ቫልደሲ ኡርኪዛ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ለድርጅቱ ላለፉት 70 ዓመታት ላደረገችው ጠንካራ ድጋፍና አህጉራዊ አመራር አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
በዕለቱ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና በኢንተርፖል መካከል የተደረገው የትብብር ስምምነት የሀገሪቱን የሕግ አስከባሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የማሰልጠንና የመደገፍ አቅም እንደሚያሳድግ ጠቁመዋል፡፡
አህጉራዊና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ መከላከል አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ የአፍሪካ ኢኮኖሚ እድገት የዓለም አቀፍ ወንጀለኞችን ትኩረት እየሳበ በመሆኑ ድንበር ተሻጋሪ የጋራ እንቅስቃሴዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ለዚህም ኢንተርፖል የመረጃ ቋቶቹን ለቀጣናው የሕግ አስከባሪዎች ተደራሽ በማድረግና አቅምን በመገንባት ረገድ የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡