አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከታሪካዊ ቁጭት ወደ ብሔራዊ ድል የሚያሸጋግር መሠረታዊ ጉዳይ ነው አሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅቶች፡፡
የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ያጣችው የባህር በር የሚያስቆጭ እና ምላሽ የሚገባው ነው፡፡
የሕዳሴ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ሱራፌል እሸቱ እንደገለጹት÷ ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ሀገርን መምራት በሚል ሽፋን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ግብ አንግቦ ሲሰራ ቆይቷል።
ቡድኑ ኢትዮጵያ የባህር በሯን እንድታጣ በማድረግ፣ ከኢትዮጵያውያን አዕምሮ የማይወጣና ዘመን የማይሽረው ታሪካዊ ክህደት መፈጸሙን በምሳሌነት አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም ዜጎች ስለ ባህር በር ምንም ዓይነት ሃሳብ እንዳይሰጡ ገደብ በመጣል፣ ትውልዱ ስለ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት እውቀት እንዳይኖረው በማድረግ አምባገነናዊነቱንና ለብሔራዊ ጥቅም ግድ የሌለው መሆኑን በተግባር አሳይቷል ነው ያሉት።
ለዚህም የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ትልቅ ማሳያ መሆኑን በመጥቀስ የባህር በር ጉዳይ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የመላው ህዝብ፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችና የሌሎችም አካላት የጋራ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል ዮሃንሰ መኮንን በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በመልክአ-ምድራዊ አቀማመጥ፣ በሕዝብ ቁጥር እንዲሁም በሕጋዊ መስፈርት የባሕር በር ባለቤት መሆን እንዳለባት ግልጽ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ነጥሎ ማየት እንደማይቻል በማንሳት የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ተገቢነት ያለውና ፍትሐዊ ጥያቄ መሆኑን አብራርተዋል።
የመደመር መንግሥት ሀገሪቱን መምራት ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ የባሕር በር ጉዳይ ዋና አጀንዳ እንዲሆን በማድረግ፣ ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ተግቶ እየሠራ መሆኑን በማንሳት ኢትዮጵያውያን በዓድዋ እና በሕዳሴ ግድብ እንዳደረጉት ሁሉ ለባሕር በር ጥያቄ ስኬት በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ያላት የተፈጥሮ ሀብት ከራሷ አልፎ ለቀጣናው ሀገራት የሚተርፍ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አበራ በቀለ ናቸው።
ታሪካዊ ጠላቶች በሴራ ኢትዮጵያ የባሕር በሯን እንድታጣ ማድረጋቸው ትክክል እንዳልነበር መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ለቀጣናው ሀገራት ጭምር ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አንስተው ጥያቄው የሁሉም ፓርቲዎች የጋራ ሀገራዊ አጀንዳ ነው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።