የሀገር ውስጥ ዜና

የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ “ምቹ-ሚዛን”አዲስ የዲጂታል ፋይናንስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

By Mikias Ayele

October 30, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ከሸሪዓ መርሆዎች ጋር የሚስማማ “ሚቹ-ሚዛን” የተሰኘ አዲስ የዲጂታል ፋይናንስ መተግበሪያ በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

በባንኩ የወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ኮፕባንክ አልሁዳ አማካኝነት የሚሰጠውና በክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ የሚደገፈው መተግበሪያው ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ንግዶች የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የታለመ ነው።

በመደበኛ አገልግሎት ነጋዴዎች ከእምነታቸውና ከእሴቶቻቸው ጋር የሚጣጣሙ የፋይናንስ አማራጮችን በማግኘት ረገድ የሚያጋጥማቸውን ችግር ይፈታል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም መተግበሪያው በዋስትና የሚያስይዙት ንብረትና የተመዘገበ ንብረት ባለመኖሩ መደበኛ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚገጥማቸውን ችግር በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።

የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ደርቤ አስፋው በዚህ ወቅት÷ ዓላማችን የዲጂታል ቴክኖሎጂን ተደራሽነትና ቅልጥፍና ከሸሪዓ መርሆዎች ጋር ከሚስማሙ የፋይናንስ አሠራሮች ጋር በማጣመር ንግዶችን ፋይናንስ በማድረግ የሚያስፈልጓቸውን አቅርቦቶች፣ ገበያዎችና ዕድሎች እንዲያገኙ መርዳት ነው ብለዋል።

“ሚቹ-ሚዛን” ከሸሪዓ መርሆዎች ጋር በሚስማማ የኢ-ኮሜርስ አገልግሎት አማካኝነት፣ ደንበኞችን የሸሪዓን መርሆዎች ባከበረ የፋይናንስና የግዢ ሂደት እንዲገዙ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙኒር ዱሪ በበኩላቸው÷ በሙከራ ትግበራ ላይ የነበረው ሚቹ-ሚዛን ከ200 ሚሊየን ብር በላይ ከሸሪዓ መርሆዎች ጋር የሚስማማ ፋይናንስ ከ4 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች ማቅረቡን ጠቁመዋል፡፡

ሚቹ-ሚዛን ለተለያዩ የንግድ ዓይነቶች የተዘጋጁ ሁለት የፋይናንስ ምርቶችን ማለትም “ሚቹ-ሚዛን ዑስራ” እና “ሚቹ-ሚዛን ታጂር” በሚል የብድር አገልግሎትን ለሴቶች እና ወጣቶች እንደሚያቀርብ አመላክተዋል፡፡

በአቤል ነዋይ