የሀገር ውስጥ ዜና

የሰው ልጅ የአኗኗር ክብርን የጠበቀ የኑሮ ዘይቤ የመፍጠሩ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል — ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By betelhem girma

November 01, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆኗ ያረጁ አካባቢዎችን በማልማት የሰው ልጅ የአኗኗር ክብርን የጠበቀ እና ከዓለም ጋር የሚወዳደር የኑሮ ዘይቤ የመፍጠር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡

በዛሬው ዕለት በቦሌ ክፍለ ከተማ የተገነባው የቦሌ ሹቡ ኤጀርሳ የተቀናጀ የነዋሪዎች መንደር ለልማት ተነሺዎች የማስተላለፍ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡

ከንቲባዋ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ስሟ ከፍ ብሎ እንድትሸለም የህዝብ ድጋፍና አዎንታዊ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

አካባቢው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ ለመገንባት ሲፈለግ ነዋሪዎቹ “ለሀገር አስፈላጊ ከሆነ እንፈቅዳለን” በማለት ላሳዩት ቀና ትብብር አመስግነዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በካዛንቺስና በፒያሳ ለተነሱ ነዋሪዎች መኖሪያ ብቻ ሳይሆን የሚሠሩበት ቦታ ታሳቢ ተደርጎ መሠራቱን አስታውሰው ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሽልማት ያበቃትም ይህ ማኅበራዊ መስተጋብርን ያልበተነ ሰው ተኮር አካሄድ ነው ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆኗ ያረጁ አካባቢዎችን በማልማት የሰው ልጅ የአኗኗር ክብርን የጠበቀና ከዓለም ጋር የሚወዳደር የኑሮ ዘይቤ የመፍጠር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ለልማት ተነሺዎች የተላለፈው የሹቡ ኤጀርሳ የተቀናጀ የነዋሪዎች መንደር የነዋሪዎችን የገቢ ምንጭ የሚያሳድጉና በዘመናዊ መሠረተ ልማት ለማስቀጠል የሚያስችሉ አዳዲስ አውታሮችን የያዘ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ዘመናዊ የከብቶች ማደለቢያ ሼድ፣ ሱቆች፣ የእህል መጋዘን፣ ወፍጮ ቤት፣ የሕፃናት ማቆያ እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ያካተተ መሆኑን አንስተው ይህም ለኑሮ አመቺ እንደሚያደርገው አስረድተዋል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በቤተልሔም ግርማ