ዓለምአቀፋዊ ዜና

አፍሪካ ህዝቦቿን ለመመገብ የሚያስችላትን እምቅ ሀብት ወደ ተግባር ለመለወጥ የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋታል – ማህሙድ አሊ ዩሱፍ

By Mikias Ayele

November 03, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካ ህዝቦቿን ለመመገብ የሚያስችላትን እምቅ ሀብት ወደ ተግባር ለመለወጥ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት፣ መልካም አስተዳደር እና የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋታል አሉ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ማህበር ጋር ረሃብን ከአፍሪካ ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ የሚያስችሉ ዘላቂ መፍትሔዎች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

በመድረኩ ማህሙድ አሊ ዩሱፍ÷ የአፍሪካ ህብረት በካምፓላ ዴክላሬሽን ማዕቀፍ መሰረት በአህጉሪቱ ጠንካራ እና ዘላቂ የግብርና-ምግብ ስርዓቶችን ለመገንባት እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

አፍሪካ ህዝቦቿን ከመመገብ አልፋ የዓለም የምግብ ቅርጫት ለመሆን የሚያስችላት እምቅ ሀብት እና አቅም እንዳላት አስገንዝበዋል፡፡

ነገር ግን ይህንን አቅም ወደ ተግባር ለመለወጥ የጋራ እርምጃ፣ ቀጣይነት ያለው ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት፣ መልካም አስተዳደር እና የተቀናጁ ጥረቶች ያስፈልጋሉ ነው ያሉት፡፡

ረሃብን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ፣ ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማፈላለግ እና ያደገች አፍሪካን ለመፍጠር ሀገራት በቁርጠኝነት እንዲሰሩ መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን የህብረቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

በሚኪያስ አየለ