አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ሰላምን በማጽናት እንዲሁም ልማትን በማስቀጠል ረገድ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል አሉ በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ።
በአማራ ክልል በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የተከናወኑ የመንግሥት እና የፓርቲ አፈጻጸምና የተገኙ ውጤቶችን የሚገመግም መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ ፥ በበጀት ዓመቱ የክልሉን እምቅ ሃብትና የመልማት አቅም መሰረት በማድረግ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
በዚሁ መሰረትም በሩብ አመቱ የታየው አፈፃፀም አበረታችና መልካም የሚባሉ ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም የክልሉን ሰላም በማጽናትና ልማትን በማስቀጠል ረገድ የመጣው ስኬት በህዝቡና በተለያዩ አካላት ትብብርና የተደመረ አቅም ነው ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው ፥ በከተማዋ ሁለንተናዊ የልማት ስራዎችን በማሳለጥ በስራ እድል ፈጠራ፣ በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም በሌሎችም ተግባራት ውጤታማ አፈፃፀም የታየባቸው መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም ከተማዋን በማስዋብ ለነዋሪዎቿና ለጎብኝዎቿ ምቹ ለማድረግ የተጀመረው የጣና ዳር ልማት እና የኮሪደር ልማት በጥራትና በፍጥነት እየተከናወነ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።