የሀገር ውስጥ ዜና

ለዜጎች ተጠቃሚነት የመደመር ታላቁን ስትራቴጂ እውን ለማድረግ ይሰራል -አፈ ጉባኤ ሙፈሪሀት ካሚል

By sosina alemayehu

November 05, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ለዜጎች ተጠቃሚነት ሰው ተኮር ሥራዎችን በማጠናከር የመደመር ታላቁ ስትራቴጂን እውን ለማድረግ በትኩረት ይሠራል አሉ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባኤ ሙፈሪሀት ካሚል።

አፈ ጉባኤዋ ይህን የተናገሩት እስካሁን የተከናወኑ ሥራዎችንና በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አስተባባሪ ኮሚቴና የማኔጅመንት አባላት ጋር የሥራ አፈጻጸም በገመገሙበት ወቅት ነው።

በንግግራቸውም ከመንግሥት ለውጥ ወዲህ የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ቀመር በጥናት ላይ ተመሥርቶ እንዲሻሻል መደረጉ መንግሥት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 98 የተደነገገው የጋራ ገቢዎች አስተዳደርና ክፍፍል የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጡን ምክር ቤቱ በክትትልና ግምገማ ሥራዎቹ አጠናክሮ ሊቀጥልበት እንደሚገባም ተናግረዋል።

በቀጣይም የምክር ቤቱ ዕቅድና አፈጻጸም ከታላቁ የመደመር ስትራቴጂ ጋር የተጣጣሙ መሆን እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

በ2050 ዓ.ም የተዋሀደች ፣ አምራችና የሰለጠነች ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ርዕይ ለማሳካት ሁሉም በኃላፊነት ስሜት ዜጋ ተኮር ሥራዎችን አጠናክሮ ሊሠሩ ይገባል ማለታቸውን የም/ቤቱ መረጃ ያመላክታል።