አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስንዴ ልማት የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩር፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የመስክ ምልከታ መርሐ ግብር በሀዲያ ዞን ሚሻ ወረዳ ተካሂዷል።
አቶ ኡስማን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በወረዳው የታየው የስንዴ ልማት አርሶ አደሮች ተደራጅተው በክላስተር ማልማት ከጀመሩ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል በተጨባጭ የሚያሳይ ነው። በግብርናው ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት፣ የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻልና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ግብርናውን በቴክኖሎጂና በምርምር ማገዝ ይገባል ብለዋል። ከተበታተነ አቅም ይልቅ ተደራጅቶ መንቀሳቀስ ፋይዳው ብዙ መሆኑን ገልጸው፤ የምግብ ሉዓኣላዊነቷን ያረጋገጠች ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ መንግሥት የጀመረውን የስንዴ ልማት አብዮት በበጋና በክረምት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በክልሉ በስንዴ ልማቱ የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለማስቀጠል ያሉንን በርካታ ጸጋዎች ፈትሾ ማልማት ከአመራሩ፣ ከባለሙያዎችና ከአርሶ አደሩ ብዙ ጥረት ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት ተወካይ አቶ ሽመልስ አለማየሁ በበኩላቸው፤ የክላስተር ስንዴ ዘር ብዜት ሥራ ፕሮጀክት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከ325 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችና ከፊል አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን ሚሻ ወረዳ እንዲሁም በምስራቅ ጉራጌ ሶዶ ወረዳዎች እየተተገበረ ይገኛል ነው ያሉት።
በክልሉ የሚታዩ የግብርና ልማት ክፍተቶችና የተጠቃሚዎች ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ምርምርን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ተረፈ ናቸው፡፡
በመስክ ምልከታው ላይ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ተመራማሪዎችና አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ