ቢዝነስ

ኢትዮጵያ ለዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ለምታደርገው ድርድር ተዘጋጅታለች – ወ/ሮ ያስሚን ወሃብረቢ

By sosina alemayehu

November 05, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በ8ኛው ዓለም ንግድ ድርጅት የሥራ ቡድን ስብሰባ ለምታደርገው የአባልነት ድርድር ተዘጋጅታለች አሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ያስሚን ወሃብረቢ።

8ኛው የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) የሥራ ቡድን ስብሰባ ከጥቅምት 30 እስከ ህዳር 1 ቀን 2019 ዓ.ም በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ይካሄዳል።

በዚሁ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል እንድትሆን የሚደራደረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ተደራዳሪ ቡድን ያደረገው ዝግጁነት በዛሬው ዕለት ተገምግሟል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ያስሚን ወሃብረቢ በዚሁ ወቅት ፥ለድርድሩ የተደረገው ዝግጅት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ አክለውም የኢትዮጵያ ልዑክ በስብሰባው ላይ የተቀናጀና የተናበበ ድርድር ማካሄድ አለበት ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

ተደራዳሪ ቡድኑ ከ7ኛው የሥራ ቡድን ስብሰባ ያገኛቸውን ተሞክሮዎች በመነሻነት በመውሰድ ለ8ኛው ምዕራፍ በቂ ዝግጅት ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን፤ይህም ወደ ፍጻሜው እየቀረበ ያለውን የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሂደት በእጅጉ እንደሚያፋጥነው ተጠቁሟል።