የሀገር ውስጥ ዜና

ግብፅ ለጥቅሟ ስትል በኢትዮጵያ ግድቦችን መገንባት አለባት -ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)

By sosina alemayehu

November 05, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ግብፅ ለራሷ ጥቅም ስትል ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገነቡ ግድቦችን ጭምር አብራ መገንባት መቻል አለባት አሉ -የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)።

ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገጹት ፥ የናይል ተፋሰስ ሀገራትን ትብብር ለማፍረስ ግብጾች እየሄዱበት ያለው መንገድ ኢትዮጵያን ይጎዳል ብለው በማሰብ የሚያደርጉት ነው ነገር ግን ከኢትዮጵያን ይልቅ ተጎጅ የሚሆኑት ግብፆች ናቸው።

የሕዳሴ ግድብን በሚገባው ቦታ ላይ ገንብተን ከዛ በመለስ ያለውን የግድቡን ውሃ መጠን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ግድቦችን መገንባት እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የምትጎዳ እየመሰላቸው ውሃ ላይ ትብብር እንዳይኖር ካደረጉ እኛ ለማልማት እና የውሃ ሀብትን ለመጠበቅ የማንንም ፈቃድ እና ቡራኬ አንጠብቅም ያሉት ሚኒስትሩ ትብበሩ ላይ ቢሰራ ግን ሚዛኑ ለነሱ ያደላ ነበር ሲሉ አመልክተዋል።

ኮፕሬቲቭ ፍሬም ወርክ ስምምነት ላይ በተፋሰሱ ውስጥ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች በጋራ ስምምነት ላይ ይደረስባቸዋል ቢልም ግን ኢትዮጵያ ይህንን ብትጠይቅም ግብፆች እንደሚቃወሙት አንስተዋል።

ሌላኛው ስምምነቱ ላይ የሰፈረዉ ጉዳይ የውሃውን ደህንነት መጠበቅ እና ማልማት የሚል ሲሆን በሶስተኛ ደረጃ የተቀመጠው ደግሞ መረጃ መለዋወጥ ነው ነገር ግን ግብጽ ስምምነቱን አፍርሳለች ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ግብጽ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰሩ የልማት ስራዎች ላይ አስተዋጽኦ ማበርከት ግዴታዋ ነው ብለው ኢትዮጵያ የምትገነባቸውን ግድቦች ጭምር አብራ መገንባት አለባት ነው ያሉት።

130 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላትን ኢትዮጵያ ስትራቴጂካሊ ፍላጎቷ ምንድን ነው የሚለውን ረጋ ብለው፣ አሁን የሚያሰሙትን ጩኸት ቀንሰው የምትሻው ነገር ላይ እገዛ ማድረግ አለባቸው ፤ የኢትዮጵያ ፍላጎት አሁን ላይ ቀይ ባህር ነው እሱ ላይም ሊተባበሩ ይገባል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በእመቤት ሲሳይ