የሀገር ውስጥ ዜና

በሀገራዊ ግቦች ላይ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የጋራ መግባባት ሊኖር ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Hailemaryam Tegegn

November 06, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በረጅም ጊዜ ሀገራዊ ግቦች ላይ በገዢና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የጋራ መግባባት ሊኖር ይገባል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ “እድገትን ማስተዳደር፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአፍሪካ ኢኮኖሚ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ንድፍ አውጪዎች ናቸው” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የመደመር እሳቤ አዲስ ነገሮችን መጀመር ብቻ ሳይሆን በሌሎች የተጀመሩትንም ከዳር ለማድረስ ያለመ ነው።

ለዚህም ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለአብነት በማንሳት፤ ፕሮጀክቱ ከተፀነሰበት ጀምሮ እስከተጠናቀቀበት ድረስ አሻራቸውን ያሳረፉ አካላትን በሙሉ አመስግነዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ካለፉት ምን ተረከብኩ ከማለት ባሻገር ለቀጣይ ጥሎት ለሚያልፈው ዘላቂ አሻራ ትኩረት እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከጫፍ በተሳተፉበት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ56 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ለፈተናዎች በቀላሉ የማይበገር አሻራን ጥሎ የማለፍ አቅጣጫ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ሁለት ቁልፍ ጉዳዮችን ያቀረቡ ሲሆን፤ ገዢና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በረጅም ጊዜ ብሔራዊ ግቦች ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ዜጎች የሚፈልጉትን የፖለቲካ ፓርቲና ሀሳብ የመምረጥ መብት እንዳላቸው ገልጸው፤ በምርጫ የሚያሸንፉ ፓርቲዎች መንግሥት ሲመሰርቱ ለሀገር ጥቅም ትርጉም ያለው ስራ መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

ሌላኛው ቁልፍ ጉዳይ አዳዲስ መሪዎችን ማፍራት መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ ተተኪ መሪዎችን ማፍራት ያልቻሉ ሀገራት ፈተናዎች ውስጥ መግባታቸውን አንስተዋል፡፡

ለዚህም ወጣቶችን ወደ መሪነት ለማምጣት በትኩረት መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በመሳፍንት ብርሌ