አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ከገነቡ አምስት ሀገራት አንዷ መሆኗን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በፊት ገፆቻቸው እየዘገቡ ነው፡፡
የመደመር መንግሥት ሀገራዊ ምጣኔ ሀብትን ለማሳደግ፣ መዋቅራዊ ስብራቶችን ለመጠገንና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በርካታ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራትን አከናውኗል፡፡
መንግሥት የተከተለው የኢኮኖሚ መንገድ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ትብብር ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ በዋናነት በአምስት የምጣኔ ሀብት ምሰሶዎች ማለትም በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን እና አይሲቲ ወይም ዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ ነው።
በእነዚህ ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቅ ኢኮኖሚ እንድትገነባ አስችሏታል፡፡
ይህን የኢኮኖሚ እድገት በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶችን እና ቁጥራዊ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያን ግዙፍ የኢኮኖሚ ግንባታ መገናኛ ብዙሃን በፊት ገፆቻቸው ሽፋን ሰጥተውታል፡፡
የቢዝነስ መፅሔት የሆነው ብሉምበርግ እንደዘገበው÷ በፈረንጆቹ 2025/26 ሐምሌ ወር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 210 ነጥብ 7 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መድረሱን አስነብቧል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካሉ ግዙፍ ኢኮኖሚዎች አንዷ መሆኗን የዘገበው ብሉምበርግ÷ ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት ደግሞ ሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ጠቅሷል፡፡
ቢዝነስ ኢንሳይድ አፍሪካ በበኩሉ÷ ኢትዮጵያ በብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴር በኩል የጠቅላላ ሀገር ውስጥ ምርት (GDP) የመነሻ ዓመት ማሻሻያ( GDP Rebasing) ማድረጓን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት በህዳር ወር 210 ነጥብ 7 ቢሊየን አሜሪካን ዶላር ወይም 31 ነጥብ 86 ትሪሊየን ብር መድረሱን በመግለፅ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር የ59 ነጥብ 2 መቶ እድገት ማሳየቱን ዘግቧል፡፡
ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ አልጄሪያ እና ናይጄሪያ ደግሞ በአፍሪካ ትልቅ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት ከአንድ እስከ አራተኛ ደረጃን የያዙ ሀገራት መሆናቸውንም አስታውቋል፡፡
ሲ.ጂ.ቲ.ኤን፣ ሬውተርስ፣ ኤ.ኤፍ.ፒ፣ ሲ.ኤም.ኤን እና ቢዝነስ ዴይሊ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት በተመለከተ ሰፊ ሽፋን የሰጡ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ናቸው፡፡
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በሚኪያስ አየለ