የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ የዓባይን ጉዳይ ዘግታ ወደ ቀይ ባህር ተሸጋግራለች – ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)

By tigist gizachew

November 06, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የዓባይን ጉዳይ ዘግታ ወደ ቀይ ባህር ተሸጋግራለች አሉ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)፡፡

ሚኒስትሩ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ኢትዮጵያ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ገንብታ አጠናቃ ትኩረቷን ወደ ቀይ ባህር አዙራለች፤ አሁንም በዓባይ ጉዳይ ላይ ተጠምደው ያሉት ግብጾች ናቸው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ ያገኘችው ውጤት የባህር በር ጥያቄዎችን እንድታነሳ ምክንያት ሆነዋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዓባይን እንዳትጠቀም ግብጽ የሰራችው ሴራ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ እንድናልፍ አድርጎናል ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

ግብጽ አሁንም በዓባይ ጉዳይ ላይ ተጠምዳለች፤ ነገር ግን የዓባይን ጉዳይ ዘግተን አጀንዳችንን ወደ ባህር በር ጉዳይ አዙረናል ነው ያሉት፡፡

ግብጾች ይህን ጥያቄ ተረድተው ለማደናቀፍ ከመሞከር ይልቅ ሊያግዙ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 56 ቢሊየን ችግኞችን መትከሏን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ ይህም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ያላትን ቁርጠኝነት ያመላክታል ብለዋል፡፡

በእመቤት ሲሳይ