የሀገር ውስጥ ዜና

አፍሪካውያን ፓርቲዎች የጉባኤውን ቃልኪዳን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆን አለባቸው – አደም ፋራህ

By Yonas Getnet

November 07, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲስ አበባ በተካሄደው 2ኛው የአህጉሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ የፀደቀውን ቃልኪዳንና የጉባኤውን የአቋም መግለጫ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆን አለባቸው አሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ።

አቶ አደም ፋራህ በ2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት፤ ጉባኤው የአፍሪካን እምቅ አቅም ወደ ብልፅግናና የጋራ ዕድገት ለመቀየር የጋራ ኃላፊነት ነው።

የጉባኤውን ውጤቶች ወደ ተግባር መቀየር ቀጣይ የተጣለብን ኃላፊነት ነው ሲሉም አፅንዖት ሰጥተዋል።

የመደመር መንፈስ አህጉር አቀፍ ትስስርን ይበልጥ እንዲያጠናክር፣ የዓድዋ ድል ታሪክም ለወደፊት የጋራ ትብብርና የጋራ ግቦችን ለማሳካት ለሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት አዲስ መነሳሳት እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

ብልፅግና ፓርቲ የጉባኤውን ቃልኪዳን ለመፈጸም ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋገጡት አቶ አደም ፋራህ፣ አፍሪካውያን በየሀገራቸው የሚገኙ እህት ፓርቲዎችም የጉባኤውን ውሳኔዎችና ቃልኪዳኖች ወደ ተግባር መቀየር እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሁለተኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ለ3 ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ በዛሬው ዕለት ተጠናቅቋል።

በመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱም የጉባኤውን ቃልኪዳን በማጽደቅና በተለያዩ የትብብር ጉዳዮች ላይ የአቋም መግለጫ ይፋ ተደርጓል።

በመሳፍንት ብርሌ