አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በፈጠራ፣ በኢንቨስትመንትና በተቋማዊ ሽግግሮች እያስመዘገበችው ያለው ሁለንተናዊ እድገት ዓለም አቀፍ ትኩረትን የሳበ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
መንግሥት “በመደመር መርህ” የሀገር ውስጥ አቅምን ከዘመናዊ እውቀት ጋር ማቀናጀቱ ደግሞ በየዘርፉ ያሉ ልማቶች በፍጥነትና በጥራት እንዲከወኑ አስችሏል።
የመደመር መንግሥት ሜጋ ፕሮጀክቶችም የዚህ ጽንሰ-ሀሳብ ተጨባጭ ማሳያዎች በመሆን የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የጂኦ-ፖለቲካዊ ገጽታ ሙሉ በሙሉ የመቀየር ስትራቴጂያዊ አቅም አላቸው።
ከእነዚህም መካከል የሀገሪቱ የኩራት ማዕከል የሆነው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተጠቃሽ ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከትናንት ታሪኩ እስከ ዛሬ ድረስ በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ታሪክ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ የያዘ ነው፡፡
በውስን አውሮፕላኖች ስራውን የጀመረው አየር መንገዱ ዛሬ ላይ የአፍሪካ አቪዬሽን አውራ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ግዙፍ ተቋም ለመሆን ችሏል።
ዓለም አቀፍ ቀውሶችንና ተግዳሮቶችን በብቃት በማለፍ አፍሪካን ከቀሪው ዓለም ጋር በማስተሳሰር ረገድ አየር መንገዱ እየተጫወተ ያለው ሚና ወደር የለውም።
በተለይም አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና እውን እንዲሆንና አፍሪካውያን በአየር ላይ ያላቸውን ትስስር ለማጠናከር እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
ይህንን የትናንት ታሪክና የዛሬ ከፍታ ይበልጥ ለማቀናጀትና በዘላቂነት ለማሻገር በአቪዬሽን ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍተው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደግሞ ሌላኛው አዲስ ምዕራፍ ነው።
12 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ግዙፍ ካፒታል የሚጠይቀው ይህ ፕሮጀክት የዘመኑን እጅግ የላቁ ቴክኖሎጂዎች፣ አረንጓዴ የዲዛይን ደረጃዎችና ዘመናዊ አገልግሎቶችን የጠበቀ እንዲሆን ታቅዷል።
የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በዓመት እስከ 110 ሚሊየን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም የሚኖረው ሲሆን፤ ይህም አሁን ካለው የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅም ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ ብልጫ ያለው ነው፡፡
ኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የትራንዚት እና የንግድ ትስስር ማዕከል የሚያደርገው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በአጭር ጊዜ ውስጥ የማነቃቃት ትልቅ አቅም አለው።
በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዓለም አቀፍ ተጓዦች ወደ ሀገራችን ሲመጡ የሆቴል፣ የቱሪዝምና የሎጂስቲክስ ዘርፎች ተጠቃሚነታቸው በከፍተኛ ደረጃ ይረጋገጣል።
በተጨማሪም የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ከግንባታ እስከ አገልግሎት መስጠት ድረስ ለአስር ሺዎች ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ የስራ እድል የሚፈጥር ነው፡፡
ይህ ታሪካዊ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚነቷ ባለፈ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ማዕከልነቷን በይበልጥ አጠናክራ እንድትቀጥል የሚያስችላት ግዙፍ ምዕራፍ ነው።
በሶስና አለማየሁ
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ