አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ያለውን ፋይዳ በመረዳት ህብረተሰቡ ለዓይን ብሌን ልገሳ በጎ ፈቃደኝነቱን እንዲያሳይ የኢትዮጵያ ደምና ሕብረሕዋስ ባንክ አገልግሎት ጥሪ አቀረበ።
ዓለም አቀፉ የዓይን ብሌን ልገሳ ወር በኢትዮጵያ ለሶስተኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡
ወሩን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ደምና ሕብረሕዋስ ባንክ አገልግሎት እና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ጠቅላይ ጸሐፊ ሀጂ መስዑድ አደም÷ ሰውን መውደድ፣ ለሰው ልጅ በጎ መዋል የሁሉም ሀይማኖት አስተምሮ መሆኑን አንስተዋል።
የዓይን ብሌን ልገሳ ሰውን ከፅልመት ወደ ብርሀን የሚያመጣ ተግባር ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ደምና ሕብረሕዋስ ባንክ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር ጤናዬ ደምሴ በበኩላቸው÷ የዓይን ብሌን በተለያዩ ምክንያቶች ሊጠፋ እንደሚችል አንስተዋል፡፡
ብርሃናቸውን ያጡ ወገኖችን ብርሃናቸውን ለመመለስ እና እንደ ሀገር ያለውን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ በማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሁሉም ሰው ይህን በመገንዘብ ለዓይን ብሌን ልገሳ በጎ ፈቃደኝነቱን እንዲያሳይ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ደምና ሕብረሕዋስ ባንክ አገልግሎት በበጀት ዓመቱ 5 ሺህ ዜጎችን ቃል ለማስገባት እና 700 የዓይን ብሌኖችን ለመሰብሰብ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ወሩን በማስመልከት የተለያዩ መርሀ ግብሮች የሚካሄዱ ሲሆን የሀይማኖት አባቶች የውይይት መድረክ፣ የስልክ የጽሁፍ መልዕክት፣ የሚዲያ ዘመቻዎች እና ሌሎች መርሀ ግብሮች ይከናወናሉ።
በቅድስት አባተ