የሀገር ውስጥ ዜና

በአንድ ወር ውስጥ 16 ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆኑ

By Hailemaryam Tegegn

November 13, 2026

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአንድ ወር ውስጥ ብቻ 16 ከተሞችና መንደሮችን ከዋናው የኤሌክትሪክ መረብና ከመረብ ውጪ በሚያገለግሉ የኃይል አማራጮች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል አለ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት።

የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አንዋር አብራር እንዳሉት፤ አገልግሎቱ በ2019 በጀት ዓመት ጥቅምት ወር የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማስፋፋት የተለያዩ ሥራዎችን አከናውኗል።

በዚህም ከዋናው የኤሌክትሪክ ኃይል መረብ ጋር በማገናኘት 15 ከተሞችን፣ ከዋናው የኤሌክትሪክ ኃይል መረብ ውጪ ደግሞ የፀሐይ ኃይል አማራጭን በመጠቀም ደግሞ አንድ ከተማን በድምሩ 16 ከተሞችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

እነዚህን አካባቢዎች ከኤሌክትሪክ መረብ ጋር ለማገናኘት በዋናው መረብ 79 ነጥብ 05 ኪሎ ሜትር፣ ከመረብ ውጪ ደግሞ 0 ነጥብ 36 ኪሎ ሜትር፣ በድምሩ 79 ነጥብ 41 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ መስመር ዝርጋታ መከናወኑን አስረድተዋል።

በተመሳሳይ በዋናው የኤሌክትሪክ መረብ 189 ነጥብ 35 ኪሎ ሜትር፣ ከመረብ ውጪ ደግሞ 3 ነጥብ 95 ኪሎ ሜትር፣ በድምሩ 193 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ መስመር ዝርጋታ ሥራ ተከናውኗል።

የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማሻሻልና ለማስፋፋትም በዋናው መረብ 44፣ ከመረብ ውጪ ደግሞ አንድ፣ በድምሩ 45 ትራንስፎርመሮች ተከላ ተከናውኖ ወደ አገልግሎት መግባታቸውንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በእነዚህ አካባቢዎች አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ 5 ሺህ 103 የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎች ተገጥመው ወደ ሥራ መግባታቸውን አብራርተዋል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ