አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በኮፕ 32 ጉባኤ የአፍሪካውያንን ጥቅሞች የሚያስከብሩ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድሮችን ታደርጋለች አሉ የኮፕ 32 ፕሬዚዳንት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)።
ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከቱርኩ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቲ አር ቲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የአየር ንብረት ፋይናንስ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
የአየር ንብረት ፋይናንስ በተግባር ከሚገለጠባቸው ዘርፎች አንዱ የአየር ንብረት ኢንቨስትመንት መሆኑን ጠቅሰው፤ ሀገራት በአረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ በአረንጓዴ መሠረተ ልማት እና በአረንጓዴ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ኢንቨስት ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ያደረገችው ጥረት ለሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንደሚሆን አብራርተዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ለመቋቋም ከ98 በመቶ በላይ የሚሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይሏን ከንጹሕና ታዳሽ ምንጮች እንደምታመነጭ ጠቁመዋል።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በሚሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የደን ሽፋን መጨመር እና የአፈር መሸርሸርን መከላከል መቻሏን አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም በአረንጓዴ ከተሞች ልማት አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ወንዞችን ከብክለት በመታደግ፣ ማራኪ የመዝናኛ ስፍራዎችን በመፍጠር እና ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ ከተሞችን መገንባት መቻሉን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት ኮፕ 32ን እንደምታዘጋጅ አንስተው፣ በመድረኩ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድሮችን ጨምሮ ኢትዮጵያ የአፍሪካንና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ጥቅም የሚያስከብሩ ቁልፍ የድርድር አጀንዳዎችን እንደምታነሳ አመላክተዋል፡፡
በፓሪስ ስምምነት መሰረት የአየር ንብረት ፋይናንስ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ግፊት እንደምታደርግም ጠቁመዋል፡፡
#ኢትዮጵያ #ኮፕ_32_ኢትዮጵያ #COP31 #COP32 #COP32ETHIOPIA #fanamediacorporation
በሚኪያስ አየለ