አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ተግባራዊ ተሞክሮዋን ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ በማስፋት በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ያላትን ተፅዕኖ እያጠናከረች ትገኛለች አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት የምትመሰል ሀገር ሆናለች።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የጀመርናቸው ሥራዎች የአካባቢ ጥበቃ፣ የዘላቂ ኢኮኖሚ ዕድገት፣ የደህንነትና የብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቂያ ቁልፍ ስልቶችም እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተፈጥሮ ሀብትን ከመጠበቅ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ልማትን በማፋጠን ለትውልድ ተሻጋሪ ብልጽግናን የማረጋገጥ ብሔራዊ ንቅናቄ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ይህንኑ ተግባራዊ ተሞክሮ ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ በማስፋት በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ያላትን ተፅዕኖ እያጠናከረች እንደምትገኝ ጠቁመዋል።
በቱርክዬ አንታሊያ የኮፕ 31 ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ እያደረገች ባለው ንቁ ተሳትፎና በከፈተችው መካነ ርዕይ የአረንጓዴ ልማት ስኬቶቿንና ሀገራዊ ትዕምርቶቿን ለዓለም እያስተዋወቀች መሆኑን አንስተዋል።
በስምንት ዓመት ከ56 ቢሊየን በላይ ችግኝ የተከለችው ሀገራችን፣ በታዳሽ ኃይል፣ በኮሪደር ልማት፣ በበጋ መስኖ፣ በወንዝ ዳርቻ ልማት የማይበገር የኢኮኖሚ ሥርዓት እየገነባች ትገኛለች ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ከአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ መሪ ሚናን ከመወጣት ባለፈ አሁን ኮፕ 32ን አስተናጋጅ ሀገር መሆኗን በማንሳት በኮፕ 31 ልምዷን እያጋራችና ከዝግጅቱ ልምድ እየቀሰመች እንግዶቿን በክብር ጠርታለች ሲሉ ገልጸዋል።
ከአንድ ዓመት በኋላ የምናስተናግደው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ኢትዮጵያ የልማት ተሞክሮዋን መሬት ላይ የምታሳይበት፣ ለአየር ንብረት ፍትሕና የልማት ፋይናንስ ገቢራዊነት የምትተጋበት፣ በቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንትና በዓለም አቀፍ አጋርነት ያሉ ዕድሎችን የምታሰፋበት ታሪካዊ መድረክ ነው ብለዋል።