አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የኢንዱስትሪ መሶብ አገልግሎትን ለማስጀመር የሚያስችል የግንባታ ሥራ አስጀመረ።
የተጀመረው ሥራ የመሶብ አገልግሎት ሞዴልን መሠረት በማድረግ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት ያለመ መሆኑነው የተገለጸው።
የኢንዱስትሪ መሶብ አገልግሎትን በኮርፖሬሽኑ ሥር በሚተዳደሩ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማስጀመር ቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ዞንን እንደ ማሳያ ለመጠቀም መታቀዱም ተገልጿል።
አገልግሎቱን ለማስጀመር የሚያስፈልጉ የሕንፃ አደረጃጀት፣ የቴክኖሎጂ፣ የአገልግሎት እና የሰው ኃይል ዝግጅቶች ያሉበትን ደረጃ በኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍፁም ከተማ እና በፌዴራል መሶብ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ ዓለማየሁ በተገኙበት ተገምግሟል።
በቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የተጀመረው የማዕከሉ ዝግጅት ሥራ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ አገልግሎት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።
ከማዕከሉ አፈጻጸም የሚገኘው ልምድና ተሞክሮ የኢንዱስትሪ መሶብ አገልግሎቱን ወደ ሌሎች ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማስፋፋት መታቀዱ ተጠቁሟል።
የኢንዱስትሪ መሶብ አገልግሎት መጀመር በኢንዱስትሪ ፓርኮችና ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶችና ኢንተርፕራይዞች የመንግሥት አገልግሎቶችን የተቀናጀ እና የተቀላጠፈ ለማድረግ እንደሚያስችልም የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ