አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከካርቦን ልቀት ነፃ የሆነ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በያዘችው ሀገራዊ እቅድ ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበች ነው አሉ የዘርፉ ምሁራን፡፡
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና የሰነ-ሰብ ኮሌጅ የሰነ መንግሥትና የልማት ጥናት መምህርና ተመራማሪ ጣሰው ታደሰ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፤ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ የምግብ ሉዓላዊነትና የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሰተሳሰረ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤን (ኮፕ-32) ለማስተናገድ መመረጧ በአረንጓዴ ልማትና በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ያላትን አሰተዋጽኦ የሚያረጋግጥ ታሪካዊ እድል ነው ብለዋል።
ጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄዱ ሀገሪቱ የአየር ንብረት ተጽዕኖን ለመከላከል ላከናወነቻቸው ተጨባጭ ተግባራት እውቅና ነው የሰጠ መሆኑን አንስተዋል።
የታዳሽ ኃይል ልማትን ከቃል ኪዳን ወደ ተግባር በመቀየር ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል ከታዳሽ ኃይል ምንጮች እንደምታመነጭ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዚህ ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን ገልጸው፤ ለጎረቤት ሀገራት የታዳሽ ኃይል ኤሌክትሪክ በማቅረብ ቀጣናው ከካርቦን ልቀት የፀዳ እንዲሆን የበኩሏን ድርሻ እየተወጣች ትገኛለች ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ አየር ንብረት ተጽዕኖን በመቋቋም የሰራችውን ተጨባጭ ስራ በአግባቡ ማስተዋወቅና መሸጥ ይገባል ያሉት ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ግብርና ኮሌጅ ተባባሪ ኘሮፌሰር የሆኑት ተራማጅ ተሰፋዬ ናቸው።
ኢትዮጵያ ባከናወነቻቸው ተግባራዊ ርምጃዎች የኮፕ-32 አስተናጋጅ ሆና መመረጧን ገልጸው፤ አጋጣሚውን በመጠቀም ዓለምን ስለ አየር ንብረት ልናስተምር ይገባል ብለዋል።
በዚህ ረገድ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለአየር ንብረት ቀውስ አይነተኛ ምላሽ ሆኖ የሚጠቀስ ተሞክሮ መሆኑንና በዚህም በርካታ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ስራ ላይ ተከታታይነት ያለውን ስራ እየሰራች ትገኛለች ያሉት ተባባሪ ኘሮፌሰር ተራማጅ ተሰፋዬ፤ በዚህም የአከባቢ ስነምህዳር ተስተካክሎ መሬት ማገገሙንና የግብርና ምርትና ምርታማነት መጨመሩን አንስተዋል፡፡
የተራቆቱ መሬቶችን በማልማት ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው የስራ እድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸው፤ እንደ ሀገር የተሰራውን ስራ ለዓለም በማሳየት ሀገራችንን የማስተዋወቅና የመሸጥ ስራ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በማቴዎስ ፈለቀ
#ኢትዮጵያ #ኮፕ_32_ኢትዮጵያ #COP31 #COP32 #COP32ETHIOPIA #fanamediacorporation