የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ አወሉ አብዲና አቶ ጌታቸው ረዳ በመቐለ የተሃድሶ ሥልጠና ካጠናቀቁ የቀድሞ ታጣቂዎች ጋር ተወያዩ

By Hailemaryam Tegegn

November 16, 2026

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሥራና ክህሎት ሚኒስትር አወሉ አብዲ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በመቐለ የተሃድሶ ሥልጠና ካጠናቀቁ የቀድሞ ታጣቂዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በትግራይ ክልል መቐለ ዩኒቨርሲቲ መለስ ካምፓስ በሚገኘው የተሃድሶ ማዕከል ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፤ በማዕከሉ የተሃድሶ ስልጠናና የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ መደበኛ ማኅበራዊ ሕይወት የመመለስ ሂደት ተመልክተዋል።

ስልጠናው የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ማኅበረሰቡ በመቀላቀል መደበኛ ሕይወታቸውን እንዲመሩና በምርታማነት እንዲሳተፉ በማስቻል ለዘላቂ ሀገራዊ ሰላም ግንባታ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑ ተጠቁሟል።

አቶ አወሉ አብዲ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ስልጠናው የቀድሞ ታጣቂ ወጣቶች ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ ዘላቂነት ያለው የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩና በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ራሳቸውን እንዲችሉ ያግዛል።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በበኩሉ በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና ወጣቶችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡

የተሃድሶ ስልጠናው የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት በመመለስ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ በምርታማነት እንዲሳተፉና ለሀገራዊ ሰላምና ልማት አጋዥ እንዲሆኑ የሚያስችል ሂደት መሆኑም ነው የተገለጸው።

በግዛቸው ግርማዬ