የሀገር ውስጥ ዜና

የቀድሞ ታጣቂዎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንሠራለን – አቶ አወሉ አብዲ

By Yonas Getnet

November 16, 2026

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀድሞ ታጣቂዎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ባሉ የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እንሠራለን አሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር አቶ አወሉ አብዲ።

ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር በመቐለ የተሃድሶ ሥልጠናቸውን ያጠናቀቁ የቀድሞ ታጣቂዎችን በጎበኙበትና ከተሳታፊዎቹ ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው።

አቶ አወሉ አብዲ በዚህ ወቅት፤ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሥራ ዕድሎች መኖራቸውን ገልጸው፣ ይህም ለቀድሞ ታጣቂዎችና ለወጣቶች በቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ምቹ ሁኔታ መኖሩን ያመለክታል ብለዋል።

የሀገሪቱን የ25 ዓመት የልማት ራዕይ እውን በማድረግ ኢትዮጵያ የምትፈራ፣ የምታመርትና የምትከበር ሀገር እንድትሆን በመደመር መንግሥት እሳቤ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተስፋዓለም ይሕደጎ በበኩላቸው፤ በፌዴራል መንግሥትና በኮሚሽኑ አማካኝነት በትግራይ ክልል ዛሬ ሥልጠናቸውን ያጠናቀቁትን 7 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎች ጨምሮ ከ63 ሺህ 500 በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ሂደቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ ለሥራና ለአቅም ግንባታ የሚውል 7 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ መደረጉንም አንስተዋል።

በተጨማሪም ለምግብና ለአልባሳት የሚውል 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ መደረጉን ገልጸው በአጠቃላይ የፌዴራል መንግሥት ለተሃድሶ ሥራው 9 ቢሊየን ብር ወጪ ማድረጉን አስረድተዋል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በግዛቸው ግርማዬ