የሀገር ውስጥ ዜና

በመቐለ ከተማ የተጀመረውን የንግድ እንቅስቃሴ በዘላቂነት ለማስቀጠል ውይይት ተካሄደ

By Hailemaryam Tegegn

November 17, 2026

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመቐለ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የተጀመረውን የንግድ እንቅስቃሴ በዘላቂነት ለማስቀጠል ያለመ ውይይት አካሂዷል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ሕገወጥ ንግድን ለመከላከልና የንግዱ ማኅበረሰብ በሙሉ አቅሙ ወደ ንግድ ሥራ እንዲገባ የሚያስችሉ ጉዳዮችን ከሰባቱ ክፍለ ከተሞች የንግድና የመንግሥት አገልግሎት ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

የመቐለ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ገብረሕይወት ገ/ስላሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ በዘላቂነት ለማስቀጠል፣ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓትን ለማስፈንና ለነጋዴዎች ምቹ የሥራ ሁኔታ ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

በተለይም ሕገወጥ የንግድ አሠራሮችን መከላከል፣ የንግድ ሥርዓቱን ማስተካከልና የንግዱ ማኅበረሰብ ያለ ማንኛውም መስተጓጎል ሥራውን እንዲያከናውን በተቀናጀ መልኩ መሥራት እንደሚገባ ገልፀዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የንግድና የመንግሥት አገልግሎት ኃላፊዎች በየአካባቢያቸው ያሉ የንግድ እንቅስቃሴ ችግሮችንና ለዘላቂነቱ መፍትሔ ሊሆኑ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ መለዋወጣቸው ተመልክቷል።

የንግድ እንቅስቃሴውን በዘላቂነት ማስቀጠል ለከተማዋ ኢኮኖሚያዊ መልሶ ማገገም፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለነዋሪዎች የሸቀጦችና አገልግሎቶች ተደራሽነት ወሳኝ መሆኑም በውይይቱ ላይ ተነስቷል።

በግዛቸው ግርማዬ