የሀገር ውስጥ ዜና

የታዳሽ ኃይል አቅማችን ፤ የፀሐይ ኃይል ለገጠሩ ማኅበረሰብ ሁለንተናዊ ሽግግር

By Yonas Getnet

November 17, 2026

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት የዘመናዊ ልማት እና የማህበረሰብ  ሁለንተናዊ ሽግግር መሠረት ነው።

በኢትዮጵያ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ በገጠር የሚኖር ሲሆን፣ በዓለም ባንክ መረጃ መሠረት አብዛኛው የገጠር ማኅበረሰብ ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ርቆ ይገኛል።

ለእነዚህ አካባቢዎች ከዋናው መስመር ጋር የተገናኘ የኤሌክትሪክ መስመር መዘርጋት ከፍተኛ ወጪና ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ የፀሐይ ብርሃን አቅም መጠቀም አዋጭ መፍትሄ ነው።

የፀሐይ ኃይል ከውኃ፣ ከነፋስና ከእንፋሎት ኃይል ጋር ተጣምሮ፣ በተለይም ለገጠሩ ማኅበረሰብ በአነስተኛ ማይክሮ-ግሪዶችና በቤት ውስጥ ሶላር ሥርዓቶች አማካኝነት የኃይል ተደራሽነትን ለማሳካት ያስችላል።

ይህ በመንግሥት ብቻ የሚከናወን ሳይሆን በግል፣ በማህበር፣ አንዲሁም በመንግሥት-የግል አጋርነት ማሳካት ይቻላል፡፡ እንደ ኬንያ እና ሩዋንዳ ያሉ የቀጣናው ሀገራት ተሞክሮ ይህንኑ የሚያሳይ ነው፡፡

ኬንያና ሩዋንዳ በመንግሥት – የግል ዘርፍ አጋርነት አማካኝነት በሚሊየን የሚቆጠሩ የገጠር ቤቶችን የሶላር ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል።

የፀሐይ ኃይል አቅርቦት መስፋፋት ለገጠሩ ማኅበረሰብ ሕይወትመሻሻል ሁለንተናዊ ሽግግር ማምጣት የሚያስችል ነው። በጤና ዘርፍ የገጠር ጤና ጣቢያዎች እና ጤና ኬላዎች ክትባቶችን በማቀዝቀዣ እንዲያስቀምጡና የሌሊት የወሊድ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላቸዋል።

በቤተሰብ ደረጃም ኩራዝና የማገዶ እንጨትን በመተካት የሴቶችንና የሕፃናትን ጤና ለመጠበቅና የአካባቢ ብክለትን ለማስቀረት ያስችላል።

በትምህርት ረገድ ተማሪዎች ምቹና አስተማማኝ የብርሃን ምንጭ ስለሚያገኙ ለማጥናትና ውጤታቸውን ከማስቻሉ በተጨማሪ በዲጂታል አሰራር ትምህርት እንዲያገኙ ዕድል ይፈጥራል።

የዲጂታል ዕውቀት እንዲያገኙ እና በከተሞች ካሉ እኩዮቻቸው ያላቸውን የዕውቀት ልዩነት ለማጥበብ ብሎም እኩል ለማድረግ ያግዛል፡፡

በኢኮኖሚ ረገድ በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ የመስኖ ውሃ መሳቢያዎች፣ የእህል ወፍጮዎችና የምርት ማቀዝቀዣዎች የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ።  ለወጣቶችና ለሴቶች አዲስ የሥራ ዕድል ይፈጥራል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ፕሮግራም አማካኝነት ከዋናው መስመር ውጭ የሚገኙ ህዝቦችን የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ በርካታ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ይገኛል።

በሶማሌ ክልል የሚገነባው ጋድ-2 እንዲሁም በአፋር ክልል የሚገነባው ወራንሶ የሶላር ኃይል ማመንጫዎች መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት የሚያሳዩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የሶላር ሴል እና ፓኔል ምርትን በስፋት ለገበያና ለውጭ ንግድ የሚያቀርቡ እንደ ቶዮ፣ ኦሪጅን፣ ሉሚንቴክ ያሉ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እያመረቱ ሲሆን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ የሶላር ፓኔሎችን፣ መብራቶችን እና የቤት ውስጥ ሲስተሞችን በመገጣጠምና በማምረት የሚታወቁ በርካታ አነስተኛ ኩባንያዎች አሉ፡፡

የፀሐይ ኃይል የብርሃን ምንጭ ብቻ ሳይሆን የገጠሩን ኢኮኖሚ የሚያነቃቃና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት የብልፅግና ግብን ለማሳካት የሚስችል ሀብት ነው።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በቴዎድሮስ ሳህለ