ስፓርት

ታዳጊ አትሌቶች የኢትዮጵያን የድል ጉዞ የሚያድሱ ሀገራዊ ኩራቶች ናቸው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን

By Melaku Gedif

November 18, 2026

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ታዳጊ አትሌቶች የኢትዮጵያን የድል ጉዞ የሚያድሱ ሀገራዊ ኩራቶች ናቸው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ታዳጊ አትሌቶቹን በአካል አግኝተው ማበረታታቸውን ገልጸዋል።

ታዳጊዎቹ በአፍላ ዕድሜያቸው በዓለም መድረክ ባሳዩት ብቃትና ባስመዘገቡት ድል የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ በክብር ከፍ ማድረጋቸውን አውስተዋል፡፡

ይህ ውጤት ለመላው ኢትዮጵያውያን ደስታና ኩራት፣ ለታዳጊው ትውልድ ደግሞ ታላቅ ተስፋና ተምሳሌት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የተመዘገበው ወቅታዊ ድል ለነገው የላቀ ስኬት መነሻና መሠረት መሆኑን ጠቅሰው÷ አትሌቶቹ በራሳቸው በመተማመን፣ ህልማቸውን በማሳደግና ከዛሬው ድል የበለጠ ከፍታን በማለም ለመጪዎቹ የዓለም ሻምፒዮናዎችና ኦሎምፒክ ጨዋታዎች በበለጠ ብቃት፣ ትጋትና ቁርጠኝነት እንዲዘጋጁ አሳስበዋል።

መንግሥት በቀጣይ የስኬት ጉዟቸው የሚያስፈልጋቸውን ሁሉንም ዓይነት ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

አትሌቶቹ ብቃትና ችሎታቸውን በቀጣይነት እያዳበሩ የሀገራቸውን ስምና ሰንደቅ በዓለም አደባባይ በተከታታይ ከፍ ለማድረግ በጽናት ለድል እንዲሰለፉም አስገንዝበዋል፡፡