የሀገር ውስጥ ዜና

የአጋሮ ከተማ የኮሪደር ልማት ውበትና የሕዝቡ እንግዳ ተቀባይነት

By Yonas Getnet

November 18, 2026

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የከተማ ኮሪደር ልማት ለኢኮኖሚያዊ ሽግግርና ለከተሞች ዘላቂ ዕድገት ወሳኝ ሚና አለው አሉ የአጋሮ ከተማ ነዋሪዎች።

በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን የምትገኘው አጋሮ ከተማ እያከናወነች ያለው የኮሪደርና የመሠረተ ልማት ሥራ የከተማዋን ገጽታ ከማሳመር ባለፈ፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ለማሳደግ፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

በታሪካዊቷ አጋሮ ከተማ በቅርቡ የተከናወኑ ሰፊ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተማዋን ውብና ማራኪ ገጽታ እንድትላበስ ማድረጋቸውን ጠቁመው፣ ከተማዋ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በፍቅርና በመከባበር አብረው የሚኖሩባት፣ የአብሮነትና የሰላም ምሳሌ መሆኗንም አስረድተዋል።

የኮሪደር ልማቱ የእግረኞችንና የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ በተገቢው ሁኔታ በመለየት፣ ለሁለቱም የተመቻቹ መንገዶችን በመፍጠር የከተማዋን ገጽታና የነዋሪዎችን ዕለታዊ እንቅስቃሴ ይበልጥ ዘመናዊና ምቹ ማድረጉንም አንስተዋል።

ልማቱ በከተማዋ ያስገኘው ሁለገብ ለውጥ ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በመፍጠር፣ ዘመናዊ ሆቴሎች፣ ተቋማትና የልማት ማዕከላት እንዲገነቡ መሠረት መጣሉንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሕዳር 29 ቀን በጅማ ከተማ ለሚከበረው 21ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ለመሳተፍ ወደ አካባቢው የሚመጡ እንግዶችን በታላቅ ደስታና ፍቅር ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል።

በጅማ ከተማ የሚከበረው በዓል ከተማዋንና አካባቢውን ለበርካታ እንግዶች የማስተዋወቅና የቱሪዝም አቅሙን የማሳደግ መልካም ዕድል እንደሚፈጥርም አመልክተዋል።

በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አከባበር ዙሪያ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙ የሚዲያ ባለሙያዎችም፤ አጋሮ ከተማ በኮሪደር ልማት ያስመዘገበችው ለውጥ፣ በባህል ብዝኃነት፣ በአብሮነትና በእንግዳ ተቀባይነት ያላት ተምሳሌታዊ መሆኑን አመልክተዋል።

በወርቅአፈራው ያለው