የሀገር ውስጥ ዜና

ከጥፋቱ ያልተማረው ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድንና የጦርነት አዙሪት

By Melaku Gedif

November 18, 2026

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ታሪክ መማር ለሚፈልጉ አካላት ሁነኛ አስተማሪ ነው፤ መማር ለማይፈልጉት ደግሞ በተደጋጋሚ የስህተት አዙሪት ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት በመሆን ውድቀታቸውን ሊያፋጥን ይችላል፡፡

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሕገ ወጡ ሕወሓት ቡድን በሰሜን እዝ ላይ የደረሰው ጥቃት፣ የሁለት ዓመት ጦርነት መነሻ ሆነ። ያ አስከፊ ጦርነት የበርካታ ዜጎች ሕይወት እንዲቀጠፍ፣ የአካል ጉዳት እንዲደርስ እንዲሁም ለበርካታ ንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል።

ሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን ጤና ተቋማት እንዲወድሙ፣ ት/ቤቶች እንዲፈርሱና እንዲዘጉ እንዲሁም ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲፈናቀሉ ከማድረግ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስከትሏል።

የዚህ ሁሉ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ተጎጂዎችም በመጀመሪያ የትግራይ ሕዝብ፣ ከዚያም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።

ከአስከፊው ጦርነት በኋላ የፕሪቶሪያ ስምምነት በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም ተፈረመ። ስምምነቱ በቋሚነት ተኩስ ማቆምና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ያለመ ነበር።

ስምምነቱ ቡድኑ ትጥቅ እንዲፈታ፣ ሕዝቡ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ እንዲሁም ለመልሶ ግንባታና ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ለሚደረገው ጥረት ትልቅ ዕድል የፈጠረ ነው። ይሁን እንጂ ሕገ ወጡ ሕወሓት ይህንን ወርቃማ ዕድል አልተጠቀመበትም።

ያለ ጦርነት መኖር የማይችለው ሕገ ወጡ ሕወሓት በሐምሌ ወር 2018 ዓ.ም የፕሪቶሪያው ስምምነት “ሞቷል” ሲል በማወጅ ከነሐሴ ጀምሮ በድንበር አካባቢዎች ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ አድርጓል።

ይባስ ብሎም ሕገ ወጥ ቡድኑ በመስከረም ወር 2019 ዓ.ም ላይ በክልሉ ያሉ ሦስት አውሮፕላን ማረፊያዎችን ተቆጣጠረ። ይህን ተከትሎም የአፍሪካ ሕብረት የሕገ ወጡ ቡድኑ ድርጊት የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ መሆኑን አስታውቋል።

ይህም የሕገ ወጡ ሕወሓት ቡድን አራተኛው የጦርነት ሙከራ ሆኖ ተመዘገበ። በዚህ ሁሉ መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰላም ጥሪያቸውን አላቆሙም።

በጉዳዩ ላይ በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ መሪዎችና ድርጅቶች መጥተው የሚሄዱ መሆናቸውን፣ ነገር ግን ሕዝብ እንደሚቀጥል አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።

ስለ ክልሉ ተተኪ ትውልድ ሲናገሩም፣ ወጣቶች ትጥቅ በመፍታት ፈንታ ለውጊያ በግዳጅ እየተመለመሉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ድርጊቱ ቡድኑ የትግራይ ሕዝብ በጦርነት አዙሪት ውስጥ እንዲኖርና ቡድኑ ሥልጣኑን እንዲያራዝም የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደሌለ አመላካች ነው።

ቀደም ባሉት ጊዜያትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለትግራይና ለትግራይ ሕዝብ ልማት እንጂ ጦርነት እንደማያስፈልግ በተለያዩ መድረኮች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።

እንደሚታወቀው ለእያንዳንዱ የተከፈተ ጦርነት፣ ሕገ ወጡ ቡድን ኃላፊነቱን አይቀበልም፤ የሰዎችን ሕይወት ያሳጣውን ጦርነት በይቅርታ ሳይሆን በሌላ ክስና በተጨማሪ ግጭትና ጦርነት ለመሸፈን ይፍጨረጨራል እንጂ።

ሕገ ወጥ ቡድኑ ከጥፋቱ የማይማር የጥፋት ኃይል ነው። ከጥፋት የማይማር ድርጅት ማለት፣ ያለፈውን ስህተት እንደ ትምህርት ወስዶ በመሻሻል ፈንታ ስህተቱን እንደ ማስረጃ ለሌሎች የሚያቀርብ ነው።

በጦርነት ሁልጊዜ የሚጎዳው ሕዝብ ነው። የተፈናቀለ ቤተሰብ፣ ልጆቹን በጦርነት ያጣ ሕዝብ፣ የተዘጋ ትምህርት ቤት፣ ያልተሰበሰበ ሰብል፣ የተቀጨ ሕልም፣ የጨለመ ተስፋ… ይህ ሁሉ የሕዝብና የትውልድ ጉዳት ነው።

ሰላም በቅጽበት ሊገነባ የሚችል ነገር አይደለም፤ ከሐቀኛ ውይይት፣ ንግግር፣ ድርድርና ግምገማ ይነሳል። ድርጅት ወደ ሕዝቡ ቀርቦ “ተሳስተናል፣ በጦርነት ውድ ዋጋ ከፍላችኋል፣ ይቅርታ” ሲል ብቻ ነው አዲስ ምዕራፍ የሚከፈተው።

ሕገ ወጡ ሕወሓት ግን ለዚህ የተፈጠረ ቡድን አይደለም፤ ቡድኑ የሕዝብ ሕመም የማይሰማው፣ በሕዝብ ስም የሚነግድ የለየለት ጸረ ሕዝብ ነውና።