የሀገር ውስጥ ዜና

በመቐለ ከተማ ባለፉት 30 ቀናት ሰላምን በማስፈን እና ተቋማትን ወደ መደበኛ ሥራ በመመለስ ረገድ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል – ሺሻይ አማረ (ዶ/ር)

By Yonas Getnet

November 20, 2026

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በመቐለ ከተማ ባለፉት 30 ቀናት ሰላምን በማስፈን፣ መንግሥታዊ ተቋማትን እና የንግድ እንቅስቃሴዎችን ወደ መደበኛ ሥራ በመመለስ ረገድ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል አሉ በትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የመቀሌ ከተማ ከንቲባ ሽሻይ አማረ(ዶ/ር)።

የከተማ አስተዳደሩ ያለፉት 30 ቀናት የሥራ አፈጻጸምን ከተለያዩ ቢሮዎች ጋር በገመገመበት ወቅት እንደተመላከተው፣ መንግሥታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥራ በመጀመራቸው ሠራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰው የደመወዝ ክፍያ እንዲፈጸምላቸው ተደርጓል።

ሆኖም ሠራተኞች የሥራ ሰዓትን አክብሮ በመግባት ረገድ ውስን ክፍተቶች መኖራቸው በግምገማው ተነስቷል።

በንግዱ ዘርፍም በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እንቅስቃሴዎች ወደ መደበኛ ሁኔታ መመለሳቸው፣ እንዲሁም መሠረታዊ ሸቀጦች እና ነዳጅ ወደ ከተማዋ መግባት መጀመራቸው የተሻለ የኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲፈጠር አስተዋጽኦ አድርጓል።

ከዚህ ባለፈ የመንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ የከተማዋን አውቶቡስ ተርሚናል በመክፈት፣ ወደ መቀሌ የሚገቡ እና የሚወጡ ጉዞዎች ሰላማዊ እና ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ከፍተኛ ሥራ ማከናወኑ ተገልጿል።

በጸጥታው ዘርፍ ከባድ ወንጀሎችን በመከላከል የከተማዋን ሰላም ለማረጋገጥ፣ ወጣቶችን በማደራጀት እና ሕዝቡን በማሳተፍ ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት አካባቢን የመጠበቅ ሥራዎች መከናወናቸው ተጠቅሷል።

ሁሉም ቢሮዎች የተቀናጀ አሠራርን በመከተል ሕዝቡን በተሻለ ብቃትና ትጋት እንዲያገለግሉ ከንቲባው ማሳሰባውቸን የዘገበው ኢዜአ ነው።