አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በመቐለ ከተማ ለሥራ እድል ፈጠራ የሚሆን የዲጂታል ምዝገባ እየተከናወነ ነው አሉ በትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሺሻይ አማረ(ዶ/ር)።
የመቐለ ከተማ ባለአደራ አስተዳደር ያለፉትን 30 ቀናት አፈጻጸም ገምግሟል።
ከንቲባ ሺሻይ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ የቀድሞ ታጣቂዎች በመቐለ የኮሪደር ልማት የሥራ ዕድል ፈጠራ ውስጥ ይካተታሉ።
በመቐለ ለመሰል የሥራ እድል ፈጠራ የሚሆን የዲጂታል ምዝገባ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
ይህ ዲጂታል ምዝገባ የከተማዋን ወጣቶች በልማት ሥራዎች ለማሳተፍ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ የቀድሞ ታጣቂዎች በኮሪደር ልማት ሥራ ተካትተው ሥራውን እንዲጀምሩ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑንም አመልክተዋል።
የባለአደራ አስተዳደሩ የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣቱን የሚያረጋግጠው የክልሉን ሕዝብ ለምርጫ ምቹ ምህዳርን እውን ማድረግ ሲችል መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ለዚህም ሕዝቡ የመረጠውን መንግሥት አቋቁሞ ለመመልከት የባለአደራ አስተዳደሩ የተቻለውን እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
በአሸናፊ ሽብሩ