አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በሲቪል አቪዬሽን ዘርፍ ያስመዘገበችው ዕድገት የሚደነቅ ነው አሉ የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ፕሬዚዳንት ቶሺዩኪ ኦኑማ።
በካናዳ ሞንትሪያል እየተካሄደ ከሚገኘው 7ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ጉባዔ ጎን ለጎን ኢትዮጵያና የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን በጋራ ያዘጋጁት መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ፕሬዚዳንት ቶሺዩኪ ኦኑማ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ኢትዮጵያ በሲቪል አቪዬሽን ዘርፍ ያስመዘገበችው ዕድገት የሚደነቅ መሆኑን አውስተዋል።
የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ፍሎረንት ሰርጌ በበኩላቸው ÷ ዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት አባል ሀገራት በድርጅቱ ምክር ቤት አባልነት ምርጫ ለኢትዮጵያ ድምጻቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ ያላትን ታሪካዊ ሚና በማስታወስ በዘርፉ እያከናወነች ያለውን ተጨባጭ ሥራ ያብራሩት ደግሞ በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ቴዎድሮስ ግርማ ናቸው።
አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ብቸኛ እጩ ሆና እንድትቀርብ ውሳኔ ያሳለፉ የአፍሪካ ሀገራትን ያመሰገኑ ሲሆን÷ ሁሉም የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት አባል ሀገራት በምርጫው ድምጻቸውን ለኢትዮጵያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የም/ቤት አባላት ምርጫ ዛሬ እንደሚካሄድ መገለጹንም በካናዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመለክታል።