አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2019 በጀት ዓመት 36 ነጥብ 2 ሚሊየን የተማሪና የመምህር መምሪያ መጻሕፍት ታትመው በመላ ኢትዮጵያ መሰራጨት ጀምረዋል አለ የትምህርት ሚኒስቴር።
በሚኒስቴሩ የትምህርት ልማት ዘርፍና የሥርዓተ ትምህርት ማበልጸጊያ ተወካይ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አበበ ጋረደው (ዶ/ር)÷ መጻሕፍት ለመማር ማስተማር ሒደትና ለትምህርት ጥራት ወሳኝ ግብዓት መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የመማሪያ መጻሕፍትን ለተማሪዎች አንድ ለአንድ ለማዳረስ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ተማሪዎች በቂና ጥራቱን የጠበቀ መጻሕፍትን በማሳተም አንድ ለአንድ ማዳረስ መቻሉን አስታውሰዋል።
ሚኒስቴሩ ከ2018 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ለቅድመ አንደኛ፣ ለ1ኛ እና ለመካከለኛ ደረጃ ተማሪዎች የመማሪያ መጻሕፍትን አንድ ለአንድ ለማዳረስ ልዩ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ መሠረት በ2019 ዓ.ም 36 ነጥብ 2 ሚሊየን የተማሪና የመምህር መምሪያ መጻሕፍትን በማሳተም ወደ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እያጓጓዘ መሆኑን አብራርተዋል።
ከታተሙት መጻሕፍት አብዛኞቹ ወደ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች መድረሳቸውን ጠቁመው÷ ክልሎችም መጻሕፍቱን ተረክበው ወደ ትምህርት ቤቶች የማሰራጨት ሥራ መጀመራቸውን አመልክተዋል፡፡
ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የታተሙትን መጻሕፍት በወቅቱ ወደየ ት/ቤቶች በማሰራጨት ለተማሪዎች እንዲደርሱ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል፡፡