የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ እና አሜሪካን የኢኮኖሚ ግንኙነት ማጠናከር ያለመ ምክክር ተካሄደ

By Hailemaryam Tegegn

November 21, 2026

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና አሜሪካ የንግድ ዲፕሎማሲን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በአሜሪካ የንግድ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ረዳት ጸሃፊ ማርክ ሚሼል ከተመራ የልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ንግድን ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ለግል ዘርፍ አጋርነቶች አዳዲስ ዕድሎችን በመፍጠርና የንግድ ዲፕሎማሲን በማሳደግ የሀገራቱን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የተመዘገቡ ውጤቶችን በተመለከተ ለልዑካኑ ገለጻ የተደረገ ሲሆን፤ የአሜሪካ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ ሀሳብ ተለዋውጠዋል፡፡

ምክትል ረዳት ጸሃፊው በዚሁ ወቅት፤ የአሜሪካ የንግድ መስሪያ ቤት የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት ለማጠናከርና የአሜሪካ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያላቸውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

ሁለቱ ወገኖች በቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ የሀገራቱን የኢኮኖሚ ትብብር ለማጠናከር ወሳኝ እድል ነው መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ የሚሆን ፋይናንስ ለማሰባሰብ በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ የአሜሪካ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ለሚያደርጉት ተሳትፎ እውቅና ሰጥተዋል፡፡

ይህንን ተነሳሽነት ወደፊት ለማራመድና የአሜሪካን ተሳትፎ ለማጠናከር ቀጣይነት ያለው ትብብር አስፈላጊ ነው ማለታቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡